በሐረሪ ክልል የትምህርት ቤት ማስፋፊያ ፕሮጀክቶች በመጓተታቸው በትምህርት አሰጣጥ ላይ ተጽዕኖ አሳድሯል

77
ሐረር ታህሳስ 11/2011 በሐረሪ ክልል ከ15 ሚሊዮን ብር ወጪ የሚካሄዱት ትምህርት ቤቶች ማስፋፊያ ፕሮጀክቶች ለሦስት ዓመታት በመጓተታቸው በትምህርት አሰጣጥ ላይ ተጽዕኖ እንደፈጠረባቸው መምህራንና ወላጆች ተናገሩ። የክልሉ ቤቶች ልማትና መንግሥት ኮንስትራክሽን ኤጀንሲ ግንባታውን ያጓተቱት ሥራ ተቋራጮችን ውል በመሰረዝ  ለሌሎች ማስተላለፉን  ገልጿል። በክልሉ በ2008 ተጀምረው ግንባታቸው ያልተጠናቀቁት የራስ መኮንን፣ የጀግኖችና የሴና አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ማስፋፊያ ፕሮጀክቶች ናቸው። ከፕሮጀክቶቹ አንደኛው በሌላ ሥራ ተቋራጭ ግንባታውን የቀጠለ ሲሆን፣ የሁለቱ ትምህርት ቤቶች ግንባታ ከተቋረጠ  ከአንድ ዓመት በላይ መሆኑን አስተያየት ሰጪዎቹ ይገልጻሉ። የራስ መኮንን አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ሼዙ መሐመድ ግንባታው በዘጠኝ ወራት ይጠናቀቃል የተባለው ፕሮጀክት ባለመጠናቀቁ በሁለት ፈረቃዎች ለማስተማር የተያዘውን ዕቅድ በአንድ ፈረቃ ለመስጠት ተገደናል ይላሉ። ፕሮጀክቱ ባለመጠናቀቁ የተማሪዎች ቁጥር መጨመሩን በዚህም ለተማሪዎች የሚሰጠውን ምዘና ለመለካትና ለመቆጣጠር ተቸግረናል ያሉት የራስ መኮንን ትምህርት ቤት የፊዚክስ መምህር ዘላለም ጉልላት ናቸው። የጀግኖች ትምህርት ቤት ምክትል ርዕሰ መምህርት ዙፋን ካሳ የፕሮጀክቱ መጓተት የተማሪዎች ቅበላ አቅማቸውን አናሳ እንዳደረገባቸው ይናገራሉ። ግንባታው ይጠናቀቃል ብለን የተቀበልናቸው የአንደኛና ሁለተኛ ክፍል ተማሪዎች በአንድ ክፍል እስከ 80 ተማሪዎች እያስተናገዱ መሆናቸውን ገልጸው፣ ችግሩ የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ አዳጋች ስለሚያደርገው መፍትሄ ሊሰጥበት ይገባል ብለዋል። የጀግኖች ትምህርት ቤት የወላጅ መምህር ኅብረት ኮሚቴ አባል አቶ ሉሉ ጥላሁን "የግንባታው መቋረጥ በትምህርት ሥራውና በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ በሚያስከትለው ተፅዕኖና መፍትሄ እንዲያገኝ በተደጋጋሚ ጊዜ ለትምህርት ቢሮና ለወረዳ ብናመለክትም፤ አፋጣኝ ምላሽ አላገኘንም" ይላሉ። በአሁኑ ወቅት ግን ለሌላ ሥራ ተቋራጭ ተሰጥቶ ግንባታው መቀጠሉን እየተመለከትኩ ነው ሲሉም ተናግረዋል። የክልሉ መንግሥት በፕሮጀክቶች ክትትል ማነስ ሳቢያ የሚያጋጥሙትን የክፍል ጥበትና የጥራት ችግሮችን ለማቃለል ትኩረት እንዲሰጥም ጠይቀዋል። የክልሉ ትምህርት ቢሮ የፕላንና ፕሮግራም ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ከበደ ሙላቱ ተጠይቀው ቢሮው  የማሳወቅ፣ የክልሉ ቤቶች ልማትና መንግሥት ኮንስትራክሽን ኤጀንሲ ደግሞ ክትትል የማድረግ ኃላፊነት ስለተሰጣቸው በሥራው ላይ ክፍተት ፈጥሯል ብለዋል። የፕሮጀክቶቹ  መጓተት በትምህርት ቅበላም ሆነ በመማር ማስተማር ሂደት ላይ ችግር በመፍጠሩ፤ በአሁኑ ወቅት በሥራ ተቋራጮች ላይ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን አስታውቀዋል። የክልሉ ቤቶች ልማትና መንግሥት ኮንስትራክሽን ኤጀንሲ ኃላፊ አቶ ኢሊ አብዱረሂም ''የትምህርት ቤቶቹ የማስፋፊያ ግንባታ ሥራ በኮንትራክተሮች የአቅም ውስንነትና በሚያቀርቡት የግንባታ ቁሳቁስ የዋጋ ንረት ሥራውን ማጠናቀቅ አልቻሉም'' ብለዋል። ኅብረተሰቡ የሚያነሳቸውን ጥያቄዎችን ለመመለስና የኮንስትራክሽን አስተዳደር በሚያስቀምጠው መመሪያ መሠረት የጀግኖች ትምህርት ቤት ግንባታ ሥራው ለሌላ የሥራ ተቋራጭ ሲሰጥ፣ ለሁለቱ ትምህርት ቤቶች ማስፋፊያ ፕሮጀክቶች ጨረታ የማውጣት ሂደት እየተጠናቀቀ መሆኑን ገልጸዋል። ፕሮጀክቶቹ በዚህ በጀት ዓመት ሙሉ ለሙሉ ተጠናቀው በመጪው የትምህርት ዘመን ለአገልግሎት እንደሚበቁ አቶ ኢሊ አስታውቀዋል። በሐረሪ ክልል 102 የመንግሥት አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችና ከሁለት ሺህ በላይ መምህራን ይገኛሉ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም