በኢትዮጵያና ሱዳን መካከል ያለው አጋርነትና ትብብር ቀጠናውን ማስተሳሰር ይችላል- ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን

86
ካርቱም 11/2011 በኢትዮጵያና ሱዳን መካከል ያለው አጋርነትና ትብብር ምሳሌ በመሆን ቀጠናውን ማስተሳሰር እደሚችልየኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ተናገሩ። በሱዳን ይፋዊ የስራ ጉብኝት ላይ የሚገኙት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዛሬው ውሎ ከሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር፣ ከምክትል ፕሬዝዳንትና ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንት ጋር በሁለቱ በአገራቱ የሁለትዮሽ ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል። ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ወቅት እንዳሉት ምክክራቸው የሁለቱን አገራትና ህዝብ ታሪካዊ ወዳጅነት በምን አይነት መልኩ መጠናከር አለበት የሚል ጉዳይ ላይ ያተኮረ ነው። ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ሁሉን አቀፍ የለውጥ እንቅስቃሴ ውስጥ መሆኗን  በመግለጽ “ሪፎርሙ በፖሊቲካ አለመግባባት ከሚናጥ አገርና ቀጠና ወደ ሰላማዊ የፖሊቲካ ውድድር መሸጋገርን ያካትታል” ብለዋል። ለህዝቦቻቸው ደህንነትና ብልጽግና የሚያመች የተረጋጋ ሰላምና ልማት ማምጣት ለሁለቱም አገራት ቀዳሚ በመሆኑ በጋራ መሥራት ይኖርባቸዋል ብለዋል። ከዚህ በፊት የነበሩትን የትብብር መስኮች ማደስ ይገባል ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ማድረግ ከተቻለ የሁለቱ አገራት ትብብር ምሳሌ ከመሆን አልፎ ቀጠናውን የማስተሳሰሪያ መንግድ መሆን ይቻላል ብለዋል። ይሄን ለማረጋገጥም  የተጠናከረ ትብብር እንደሚያስፈልግ አብራርተዋል። ሁለቱ አገራት እስከ ዛሬ ተቀራርቦና ተባብሮ በመስራታቸው ብዙ ተጠቅመዋል ያሉት የሱዳኑ ምክትል ፕሬዝዳንት ኦስማን ሙሃመድ ኪብሪ፤ አንዱ አገር ከሌላው የሚፈልገው ብዙ ነገር በመኖሩ እንደገና መታደስና መነቃቃት ይገበዋል በማለት መንግስታቸው ያለውን ቁርጠኝነት  አረጋግጠዋል። ለሶስት ቀን ይፋዊ የስራ ጉብኝት ላይ የሚገኙ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ትናንት ማምሻውን ከፕሬዝዳንት አልበሽር ጋር መምከራቸው የሚታወስ ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም