የዩኒቨርሲቲው ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሥራ እንዲጠናከር ድርሻቸውን እንደሚወጡ ነዋሪዎች አረጋገጡ

65
ድሬዳዋ ታህሳስ 11/2011 የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሥራ እንዲጠናከር ድርሻቸውን እንደሚወጡ በዩኒቨርሲቲው ዙሪያ ያሉ ነዋሪዎች አረጋገጡ። ዩኒቨርሲቲው በተማሪዎች መካከል ግጭት እንዲፈጠርና ወደ ማህበረሰቡ እንዲዛመት የሚፈልጉ ሠራተኞቹን እንዲፈትሽም አሳስበዋል፡፡ በዩኒቨርሲቲው ካለፈው ማክሰኞ ጀምሮ ''መንስዔው ለጊዜው እየተጣራ ነው'' በተባለ ሁከትና ብጥብጥ የመማር ማስተማሩ ተግባሩ ተቋርጧል። ዩኒቨርሲቲው ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሥራውን ለመጀመር በዙሪያው ከሚገኙ የገንደተስፋና መርማርሳ አካባቢ ነዋሪዎች ጋር ዛሬ ተወያይቷል፡፡ ተሳታፊዎቹ ዩኒቨርሲቲው ከኅብረተሰቡ  ጋር ተቀናጅቶ ተልዕኮውን  ለማሳካት መሥራት እንደሚጠበቅበት አስገንዝበዋል፡፡ በውይይቱ ላይ የተሳተፈው ወጣት ኤልያስ አብዱላሂ በዩኒቨርሲቲው የተከሰተው ግጭት የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት ተብሎ የተቀነባበረ ሊሆን  እንደሚችል ይናገራል፡፡ ''ችግሩን ለመፍታት ከተማሪዎች መኝታ ክፍል አስተባባሪዎች እስከ ዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች ድረስ ጠንካራ ግምገማ ማድረግና እውነታውን ለህዝብ መግለፅ ይገባል'' ሲልም አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡ በዩኒቨርሲቲው ዙሪያ የሚገኙ ነዋሪዎች ከዩኒቨርሲቲው ሸሽተው የወጡ 130 ተማሪዎችን መመገባቸውን ገልጾ፣ ከዚያም አልፎ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሥራውን እንዲቀጥል በመሥራት ላይ መሆናቸውን ተናግሯል፡፡ በዩኒቨርሲቲው ዙሪያ የሚገኙ ነዋሪዎች ሰላም እንዲሰፍንና ትምህርት እንዲቀጥል ድጋፍ እያደረግን ነው የሚሉት ወይዘሮ ሐዋ ዑስማን ናቸው፡፡ ''ዩኒቨርሲቲው የተጣሉ ተማሪዎችን በፍጥነት ማስታረቅና ሥራውን መቀጠል ሲገባው ችግሩ እንዲስፋፋ ቀዳዳ መፍጠር አልነበረበትም'' ብለዋል። የአገር ሽማግሌዎችንና የሃይማኖት አባቶችን በማሳተፍ ሰላምን ማውረድ እንደሚያስፈልግም አስተያየት ሰጪዋ ተናግረዋል። አቶ ሙሣ ጃማ የተባሉ ነዋሪ በበኩላቸው በዩኒቨርሲቲው የተፈጠረው ችግር አሳፋሪ ነው ይላሉ። ነዋሪዎች ችግሩን በዩኒቨርሲቲው ዙሪያ ወደሚኖረው ኅብረተሰብ ለማዛመትና የብሔር ግጭት ለመቀስቀስ የተደረገው ጥረት መመከታቸውንም  ገልጸዋል፡፡ ''በዩኒቨርሲቲው የሚገኘው ፌዴራል ፖሊስ ገለልተኛ ሆኖ ማገልገል፣ ብረትና ዱላ ወደ ዩኒቨርሲቲው ሲገባ መቆጣጠር ይኖርበታል'' ብለዋል፡፡ ወይዘሮ አሚና አህመድ በበኩላቸው ግጭቱን ለማብረድ ተብሎ የሚወሰደው እርምጃ መመጣጠን እንዳለበት ይገልጻሉ፡፡ በግጭቱ ሳቢያ በጅምላ የተወሰዱ ሰዎችን መለየትና ችግር የሌለባቸውን መልቀቅ እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡ የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ያሬድ ማሞ በነዋሪዎቹ የተነሱ ሃሳቦች ለዩኒቨርሲቲው ቀጣይ ሥራ ጠቃሚ በመሆናቸው ራሱን ለመፈተሸና ለማጥራት በሚያደርገው እንቅስቃሴ እንደሚጠቀምባቸው ገልጸዋል፡፡ ''በመረጃና ማስረጃ ላይ የተመሰረተ ሥራ እየተሰራ ይገኛል፤ የሚደበቅና የሚድበሰበስ አንዳችም ነገር የለም'' ሲሉም ተናግረዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ከኅብረተሰቡ ጋር ያለው ግንኙነት የሚያጠናክርባቸው ሥራዎች እያከናወነ መሆኑን  አስታውቀዋል። ነዋሪዎቹ ለሰላም መስፈን የሚያደርጉትን ጥረት እንዲያጠናክሩም ፕሬዚዳንቱ ጠይቀዋል፡፡ የድሬዳዋ አስተዳደር ፍትህ፣ ፀጥታና የሕግ ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ዩሱፍ በዩኒቨርሲቲው ሰላማዊ የመማር ማስተማሩ ተግባር እንዲጠናከር የፀጥታ አካላት፣ ዩኒቨርሲቲውና ኅብረተሰቡ ተቀናጅተው ሊሰሩ ይገባል ብለዋል፡፡ ባለፉት ሶስት ቀናት በቁጥጥር ሥር የዋሉ አካላትን በመለየት የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ እንደሚሰራና በግጭቱ ውስጥ የሌሉበት ሰዎች ተጣርተው እንደሚለቀቁም ተናግረዋል፡፡ በድሬዳዋ የፌደራል ፖሊስ አድማ በታኝ አዛዥ ኮማንደር ሂርፖ ነገሪ በበኩላቸው ፖሊስ የዩኒቨርሲቲው ሰላምና ፀጥታ አስተማማኝ እንዲሆን በገለልተኝነት እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ ''ሁሉንም በእኩልነት በኢትዮጵያዊነት እያገለገልን ነው፤ የተበላሸውን ሰላም ወደ ቦታው በመመለስ ሂደት ውስጥ ልታግዙን ይገባል'' ብለዋል፡፡ ለግጭቶችን የተለያዩ መልኮች በመስጠት ለማስፋፋት የሚሞክሩ ኃይሎች መኖራቸወን የገለጹት ኮማንደር ሂርፖ፣ ከነዚህም ወደ ዩኒቨርሲቲው ግቢ ለመግባት ሲሞክሩ በቁጥጥር ሥር የዋሉ ኃይሎች መኖራቸውን ጠቅሰዋል። ኅብረተሰቡ ያመለጡትን አሳልፎ በመስጠት እንዲተባበርም ጠይቀዋል። ዩኒቨርሲቲ በቀጣይ ተመሳሳይ ውይይት ከኃይማኖት አባቶችና ከአገር ሽማግሌዎች ጋር እንደሚያደርግም ተገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም