ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሴቶችን ተሳትፎ በቁልፍ ተልዕኮዎቻቸው እየተጠቀሙበት አይደለም

83
አዲስ አበባ ታህሳስ 11/2011 ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በቁልፍ ተልዕኮዎቻቸው ላይ የሴቶችን ተሳትፎ በሚፈለገው ልክ እየተጠቀሙበት አይደለም ተባለ። የሳይንስና የከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ይህን ያለው የዩኒቨርሲቲዎች ሴት መምህራንና አመራሮች በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ቁልፍ ተልዕኮዎች የሴቶችን ተሳትፎ ማሳደግን አስመልክቶ በአዲስ አበባ በተካሄደ ውይይት ነው። ሚኒስትሯ ዶክተር ሂሩት ወልደማሪያም ውይይቱን ሲመሩ እንዳሉት ሴቶች በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በአመራርነት፣ በምርምርና መሰል ቁልፍ ተልዕኮዎች የመሳተፍ እድላቸው በጣም ዝቅተኛ ነው። ከ50 የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎችና ኮሌጆች በአንዳቸውም ሴት ፕሬዚዳንት አለመኖሩን የጠቀሱት ዶክተር ሂሩት 18 ሴት ምክትል ፕሬዚዳንቶችና አራት ሴት ፕሮፌሰሮች ብቻ መኖራቸውን ተናግረዋል። በምርምርም ሆነ በአመራርነት የሴቶቹ ተሳትፎ ዝቅተኛ መሆን በተለያዩ ጫናዎች ምክንያት እንደሆነ ያሳያል ነው ያሉት። የነበረው "የአባታዊ የበላይነት" ባህል ጫና ማሳደሩን፣ ወንዶችም ሴቶች በቁልፍ ተልዕኮዎች ላይ ይሰራሉ የሚል እምነት እንዳይኖራቸውና ሴቶቹም አንችልም የሚል አመለካከት እንዲይዙ ማድረጉን አክለዋል። ችግሩን ለመፍታት 'በዛሬው የምክክር መድረክ መጨረሻ ላይ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሴት መምህራንና ምሁራን ሃሳባቸውን የሚለዋወጡበት ፎረም ወይም ኔትወርክ መስርተን ወደ ስራ እንገባለን' ነው ያሉት ሚኒስትሯ። በሚኒስቴሩ የሚመራው ይህ ኔትወርክ የትምህርት ተቋማቱን አሰራርና ችግሮች የሚለዋወጡበት ሲሆን በስተመጨረሻም በቁልፍ ተልዕኮዎቻቸው ላይ የሴቶችን ተሳትፎ ከማረጋገጥ አኳያ አቅደው መተግበርና አለመተግበራቸውን ለመገምገም የሚረዳ ነው። በእስካሁን ሂደት ከዩኒቨርሲቲዎች የቦርድ አባላት ግማሽ የሚሆኑት ሴቶች እንዲሆኑ ተደርጓል፤ በቀጣይም ሁሉም ከፍተኛ የትምህርት ተቋም 'ቢያንስ ሁለት ሴቶችን በቁልፍ አመራርነት ላይ እንዲያስቀምጥ ይደረጋል' ብለዋል። ይሁን እንጂ ሴቶችን ወደ አመራርነት ስናመጣ 'በኮታ' ሳይሆን ባላቸው ብቃት አወዳድረን ሊሆን ይገባል ሲሉም አክለዋል። ይህን መሰረት በማድረግ ቀደም ሲል የነበረውን የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አመራር መመልመያ መመሪያ በአዲስ መልክ እየተሻሻለ መሆኑንም ሚኒስትሯ ተናግረዋል። የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው የሴቶችን ተሳትፎ ለማረጋገጥ በርካታ አሰራሮችና ፖሊሲዎች ቢቀመጡም ሲተገበሩ አይታዩምና ተጠያቂነትን ኖሯቸው እንዲተገበሩ አመልክተዋል። ሴቶችም አንችልም የሚለውን አመለካከት ከውስጣችን አውጥተን 'መንቀሳቀስ ይኖርብናል' ሲሉም አስተያየታቸውን አክለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም