የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ 220 የጤና ባለሙያዎችን ያስመርቃል

48
ሐረር ታህሳስ 11/2011 የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የፊታችን ቅዳሜ በሕክምና ጤና ሳይንስ ያሰለጠናቸውን 220 የጤና ባለሙያዎችን ያስመርቃል። የዩኒቨርሲቲው የሕዝብና ዓለም አቀፍና  ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ዓለምሸት ተሾመ ዛሬ ለኢዜአ እንደተናገሩት ዩኒቨርሲቲው ተማሪዎችን  የሚያስመርቀው በሕክምና ዶክትሬት ዲግሪና በነርስነት ሙያዎች ነው። ከተመራቂዎቹ 173 የሕክምና ዶክተሮች፤ 47ቱ ነርሶች መሆናቸውን አስታውቀው ከጠቅላላው ተመራቂዎቹ መካከል ደግሞ 38ቱ ሴቶች ይገኙበታል ብለዋል። በዩኒቨርሲቲው በሐረር ሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በሚከናወነው የምረቃ መርሐ ግብር ላይ ከፍተኛ የፌዴራልና የክልል ባለሥልጣናት  ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል። ዩኒቨርሲቲው ባለፉት አምስት ዓመታት 598 ሐኪሞችን አስመርቋል። በአሜሪካ መንግሥት ትብብር በ1945 የተመሰረተው የግብርና ኮሌጅ፣ በአገሪቱ ግብርና ትምህርት በመስጠት ቀዳሚው የከፍተኛ ትምህርት ተቋም መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ። ዩኒቨርሲቲው በዘጠኝ ኮሌጆችና በአንድ ኢንስቲትዩቱ ውስጥ በከፈታቸው 27 በዶክትሬትና 127 ደግሞ በሁለተኛ ዲግሪ መርሐ ግብሮች ተማሪዎችን እያስተናገደ ይገኛል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም