በምስራቅ ወለጋ መስሪያ ቤቶች አገልግሎት መስጠት ጀመሩ

51
ነቀምቴ ታህሳስ 11/2011 በምስራቅ ወለጋ ዞን ለሁለት ሳምንት ያህል ተዘግተው የነበሩ  የመንግስት መስሪያ ቤቶች አገልግሎት መስጠት መጀመራቸው ተገለጸ፡፡ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና ኦሮሚያ  አዋሳኝ ወረዳዎች በተፈጠረው ግጭት ምክንያት  ነው አገልግሎት አቋርጠው የነበረው፡፡ የዞኑ አስተዳደር ጽህፈት ቤት  ተወካይ አቶ አዱኛ ጎበና እንዳስታወቁት  ከዞን እስከ ወረዳ ተዘግተው የነበሩ  የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችና ሌሎች አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ከታህሳስ  8/2011 ዓ.ም ጀምሮ  ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ ገብተዋል፡፡ በፍርድ ቤቶች መዘጋት ምክንያት በህብረተሰቡ  ደርሶ የነበረው መጉላላት ለማስቀረት  በተደረገው ጥረት ችግሩ አሁን ተቃሏል፡፡፡ ችግሩ የተቃለለው  የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የምዕራብ  ቋሚ ችሎት፣  የወረዳና የከፍተኛ ፍርድ ቤቶች  ካለፈው ሰኞ  ጀምሮ ተከፍተው አገልግሎት መስጠት በመጀመራቸው መሆኑን  የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የዳኝነት አሰጣጥ አገልግሎት የሥራ ሂደት አስተባባሪ  አቶ ፍቃዱ መኩሪያ ገልጸዋል፡፡ የጉቶ ጊዳ ወረዳ የገቢዎች ባለሥልጣን የገቢ ኦፕሬሽን የሥራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ሂካ ፋጂ በበኩላቸው የነበረው ችግር በመሥሪያ ቤቱ መዘጋት በመንግሥት ገቢ ላይ  አሉታዊ ተጽዕኖ አሳድሮ ማለፉን ተናግረዋል፡፡ በግብር ከፋዮች ላይም መጉላላት መድረሱን አስታውሰው ከወረዳው መሰብሰብ  የነበረበት  ወደ 1 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ገቢ በወቅቱ አለመግባቱንም አመልክተዋል፡፡ አስተባባሪው እንዳሉት በአሁኑ ወቅት  አንፃራዊ ሠላም በመስፈኑ ሁሉም ወደ ነበረበት ቦታ ተመልሷል፡፡ የነቀምቴ ከተማ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን  ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ቤኛ ሽራሙ በበኩላቸው በከተማው የመማር ማስተማር ሥራን ጨምሮ ሁሉም የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች  አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን አረጋግጠዋል፡፡ በከተማው አንፃራዊ ሰላም በመስፈኑ ሁሉም ወደ ነበረበት መመለሱን  የከተማው  አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ኮማንደር ግርማ አብዲሣ  አስረድተዋል፡፡ በተመሳሳይ በወለጋ ዩኒቨርሲቲ ለዘጠኝ ቀናት ተዘግቶ የነበረው የመማር ማስተማር ሥራ  ከታህሳስ  08/2011 ዓ.ም ወደነበረበት መመለሱን  ዩኒቨርሲቲው የኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን  ዳይሬክተር አቶ ያሬድ ደሣለኝ አስታውቀዋል፡፡ ከኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምዕራብ ኦሮሚያ ቋሚ ችሎት ታህሳስ 2/2011ዓ.ም  በነበራቸው  ቀጠሮ ኪሎ ሜትሮችን አቋርጠው  ከጅማ ዞን ኦሞ ናዳ ወረዳ እንደመጡ የተናገሩት  አቶ ዛክር አባጎጀም ሆኖም በነበረው ችግር አገልግሎቱን አጥተው ለእንግልትና አላስፈላጊ ወጪ መዳረጋቸውን ገልጸዋል፡፡ አሁን አገልግለቱ  በመጀመሩ ወደ ጉዳያቸው መግባታቸውን ጠቁመው  "ድርጊቱ የሚጎዳው እኛው አገልግሎት ፈላጊዎች በመሆኑ ሁሉም ለአከባቢው ሰላም  ዘብ  መቆም አለበት"ብለዋል፡፡ በምሥራቅ ወለጋ ዞን ኑኑ ቁምባ ወረዳ የጉዲና ወሊኒ ቀበሌ አርሶ አደር ገመቹ ተርፋ በበኩላቸው ከወረዳ ፍርድ ቤት ይግባኝ ይዘው  ህዳር 18/2011 ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት እንደመጡ አስታውሰዋል፡፡ ሆኖም  በዕለቱ በነበረው ሰላማዊ ሰልፍ ምክንያት  ፍርድ ቤቱ በመዘጋቱና  በኋላም ባለመከፈቱ ይግባኛቸውን ይዘው መፍትሔ ሳያገኙ ቢቆዩም አሁን ችግራቸው እየተቃለለ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ያለበቂ  ምክንያት  የመማር ማስተማሩ ሥራ ለሁለት ሳምንት  በመቋረጡ ለዓመት የተመደበው የትምህርት ክፍለ ጊዜ እየተስተጓጎለ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ  የዲጋ ወረዳ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ሱፐርቫይዘር አቶ መኮንን ጎላሳ ናቸው፡፡ ተማሪዎች ከአሳሳቾች በመራቅ  ለትምህርታቸው መትጋት እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም