በሲቪል ሰርቪስ ሴክተር መሰረታዊ ለውጥ የሚያመጣ ፍኖተ ካርታ እየተዘጋጀ ነው

181
አዳማ ታህሳስ 112011 በሲቪል ሰርቪስ ሴክተር መሰረታዊ የአገልጋይነት ለውጥ ለማምጣት የሚያስችል ፍኖተ ካርታ እያዘጋጀ መሆኑን የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን አስታወቀ። ኮሚሽኑ በፍኖተ ካርታው አዘገጃጀትና አተገባበር ዙሪያ የማደበሪያ ሀሳብ ለማሰባሰብ ከዩኒቨርስቲ ምሁራን፣ ከክልል የዘርፉ አመራሮች፣ባለሙያዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በአዳማ ከተማ እየመከረ  ነው። ከዛሬ ጀምሮ ለሁለት ቀናት በተዘጋጀው የምክክር መድረክ የኮሚሽኑ ኮሚሽነር አቶ በዛብህ ገብረየስ እንደገለጹት ፍኖተ ካርታው  ነባሩን የመንግስት ቢሮክራሲ አካሄድን ጨምሮ አሮጌ አሰራርና አደረጃጀትን በእውቀትና ክህሎት ላይ ተመስርቶ  ከለውጡ ጋር መራመድ በሚያስችል መልኩ ለመቀየር ያለመ ነው። በሲቪል ሰርቪሱ ያለበትን ችግር የዳሰሰ ጥናት የዓለም ባንክና የሀገር ውስጥ ምሁራን ን ባሳተፈ መልኩ መካሄዱን ጠቅሰው በጥናቱ ግኝት መሰረት አጠቃላይ ሴክተሩን የሚቀይር አሰራርና አደረጃጀት ለመፍጠር ጭምር እንደሆነም አመልክተዋል። መለያ የሆነውን የአሰራር፣አገልጋይነትና አደረጃጀት ሥርዓት ለመዘርጋትና ህብረተሰቡ ከኛ የሚጠብቀውን አገልግሎት እንዲያገኝ ለማስቻል ጭምር ያለመ መሆኑንም ገልጸዋል።  " እየተዘጋጀው ያለው የፍኖተ ካርታ ዓላማው በመንግስት አገልግሎት አሰጣጥ የዜጎችን እርካታ ለማምጣት፣ሲቨል ሰርቫንቱ ከፖለቲካ ነፃ ሆኖ ህዝባዊ የአገልጋይነትን መንፈስ እንዲለባስ ማድረግ ነው" ብለዋል። ብቃትን መሰረት ያደረገ የሰው ኃይል ምልመላ፣ቅጥርና ምደባ፣ማንም እንደፈለገው የሚቀጥር፣ምደባ የሚሰጥና የደረጃ እድገት ለፈለገው መስጠት እንደማይቻል ያመለከቱት ኮሚሽነሩ እውቀትና ብቃን ብቻ መሰረት ያደረገ እንዲሆን እንደሚሰራ ተናግረዋል። አስተሳሰብ፣ክህሎትና እውቀት መሰረት በማድረግ የሙያዊ አቅም መገንባትና ስልጠና መስጠት ሌላኛው የፍኖተ ካርታው የትኩረት አቅጣጫ ነው። " የአዲሱ አሰራር ተግባር ከፌዴራል እስከ ወረዳ ድረስ ያሉ አመራሮችና ባለሙያዎችን የደበዘዘውን የአገልግሎት አሰጣጥና የአጋልጋይነት መንፈስ ለመለወጥ ነው "ብለዋል። የሲቪል ሰርቪስ ሴክተር ዩኒቨርስቲን ጨምሮ በየደረጃው በሚገኙ የሥራ አመራር ኢንስቲትዩትና የአመራር አካዳሚዎች የአስተሳሰብ፣ክህሎትና እውቀት ስልጠናና አቅም ግንባታ ይሰጣል ተብሏል።   የብሪታንያ የአመራርና የሲቪል ሰርቪስ  ተቋም ተወካይና በመድረኩ ላይ ጽሑፍ ያቀረቡት አቶ አህመድ ሙሐመድ በበኩላቸው ሴክተሩ  የፖለቲካውን ርዕዮተ ዓለም አስፈፃም ሆኖ እንደነበር ተናግረዋል።   እንደ አውሮፓ አቆጣጠር ከ2006 እስከ 2011 በሀገሪቱ የተተገበሩ አዳዲስ የማሻሻያ  ሥራዎች በሲቪል ሰርቫንቱና አመራሩ ላይ መሻሻሎች እንዲመጡ ማገዙን  አመልክተዋል፡፡   ሆኖም ባለፉት ሰባት ዓመታት ማሻሻያዎቹ ተጀምረው ሳይተገበሩ የሚቀሩበት አጋጣሚዎች የተፈጠሩበት ሁኔታ መታየቱን አስረድተዋል፡፡ ለዚህም የፖለቲካውና የመንግስት ሠራተኞች ተልዕኮ በመደባለቁ ሲቪል ሰርቫንቱ በመንግስት ከተሰጠው ተልዕኮ ውጪ ይንቀሳቀስ እንደነበር  ጠቅሰዋል። ይህ በመንግስት መወዋቅር ለተፈጠረው ብልሹ አሰራር፣ሙስናና የፍትህ መጓደል ብር የከፈተ ከመሆኑም ባለፈ የህዝብ መልካም አስተዳደር ጥያቄ ውስጥ እንዲገባ መሆኑን ተናግረዋል። ለመንግስት ሠራተኞች ምንም አይነት የማነቃቂያና ምቹ የሥራ ቦታዎች ያለመፈጠር፣የሰው ኃይል ምልመላ፣ቅጥርና ምደባ አድሎዊነት የሲቪል ሰርቪሱ አገልግሎት እንዲወድቅ ምክንያት ሆኗል፡፡ እየተዘጋጀ ያለው ፍኖተ ካርታ በሀገሪቱ የሲቪል ሰርቫንት አስተሳሰብ፣አሰራርና አደራጃጀት ላይ መሰረታዊ ለውጥ የሚያመጣ መሆኑንም  አቶ አህመድ አስረድተዋል።          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም