ኢትዮ-ቴሌኮም ለዓለም አቀፍ የድምፅ ጥሪና አጭር የፅሁፍ መልዕክት የታሪፍ ቅናሽ አደረገ

75
አዲስ አበባ  ታህሳስ 11/2011 ኢትዮ-ቴሌኮም ለዓለም አቀፍ የድምፅ ጥሪና አጭር የፅሁፍ መልዕክት የታሪፍ ቅናሽ አደረገ። ነገ የሚጀምረው የታሪፍ ቅናሽ ከድምፅ ጥሪ ከ40 እስከ 10 በመቶ ከፅሁፍ መልዕክት ደግሞ የ51 በመቶ ነው። የቴኮሙ ዋና ስራ አስፈፃሚ ወይዘሪት ፍሬህይወት ታምሩ እንደገለጹት ቅናሹ የደንበኞችን ፍላጎት መሰረት ያደረገና ተቋሙ ከዓለም አቀፍ አገልግሎቶች የሚያገኘውን ገቢ የሚያሳድግ ነው። ባለፈው ሐምሌ መጨረሻ የአገር ውስጥ የአገልግሎት ታሪፍ ማሻሻያን ተከትሎ ከደንበኞች አለምአቀፉ ታሪፍም እንዲሻሻል በተጠየቀው መሰረት የተደረገ እንደሆነም ገልጸዋል። ቀደም ሲል የተደረገው ማሻሻያ 'ከውጭ የምንቀበለውን 500 ሺህ ጥሪ ወደ 800 ሺህ አሳድጎልናል' ብለዋል ዋና ስራ አስፈጻሚዋ። ጥሪዎች ከኢትዮ-ቴሌኮም ውጭ ባሉ 300 ኦፕሬተሮች እየተስተናገዱ መሆኑንና የተደረገው ማሻሻያ ህገወጥ የቴሌኮም ማጭበርበርን መከላከል እንደሚያስችል ጠቅሰዋል። ይህ ማሻሻያ የአለም አቀፍ ጥሪው ከኢትዮጵያ እስከ መዳረሻው አገር ያለውን የቴሌኮም መሰረተ ልማት ታሳቢ ያደረገ ነው።   በዚህ መሰረት በደቡብ አሜሪካ ለሚገኙ 14 አገራት የ40 በመቶ፤ ለሰሜን አሜሪካ 27 አገራትና ለአውሮፓ 25 አገራት ደግሞ የ20 በመቶ ቅናሽ ተደርጓል።   ለ37 የእስያና የመካከለኛው ምስራቅ አገራት እንዲሁም ለ10 የኦሽኒያ አገራት የ15 በመቶ ቅናሽ የተደረገ ሲሆን ለ12 የአፍሪካ አገራትም  የ10 በመቶ ቅናሽ ተደርጓል።   ከነዚህ አገራት ውጭ ባሉ አገራት ታሪፉ ባለበት እንደሚቀጥል ነው የተገለፀው።   በአጭር የፅሁፍ መልዕክትም የ51 በመቶ ቅናሽ የተደረገ ሲሆን ይህም በአንድ መልዕክት 2 ብር ከ99 ሳንቲም እንዲሆን ነው የተደረገው። አዲሱን የፈረንጆች ዓመትና የገናን በዓል ምክንያት በማድረግም ከታህሳስ 4-26 ቀን 2011 ዓ.ም አምስት አጭር የፅሁፍ መልዕክት በነጻ መላክ እንደሚቻል ተገልጿል። በተያያዘ ዜና ኢትዮ-ቴሌኮም አገልግሎት ላይ የነበሩና አሁን ጥቅም ላይ ያልሆኑ 18 ሚሊዮን የሞባይል ቁጥሮችን ከነገ ጀምሮ በድጋሚ ጥቅም ላይ እንደሚያውል አስታውቋል። ቀደም ሲል በእነዚህ ቁጥሮች ሲጠቀሙ የነበሩ ደንበኞች በድጋሚ እንዲያወጧቸው ለአንድ ወር ቅድሚያ እንደሚሰጣቸውም ተገልጿል። ቁጥሮቹ ከሁለት እስከ ሰባት ዓመት ድረስ ጥቅም ላይ ያልዋሉ መሆናቸውንና ሀብትን በአግባቡ ለመጠቀም ሲባል እርምጃ መወሰዱንም ወይዘሪት ፍሬህይወት አስረድተዋል። ለመስመር ስልክ ተጠቃሚዎች የቢል ክፍያ ስርዓቱን ለማሻሻል እየተሰራ መሆኑንና ከመጪው ጥር ጀምሮ የቅድመ ክፍያ ስርዓት እንደሚጀመር አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም