በቀድሞው የሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት አብዲ መሃመድ ዑመር ምርመራ ተጨማሪ ጊዜ ተሰጠ

53
አዲስ አበባ ታህሳስ 11/2011 በቀድሞው የሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት አብዲ መሃመድ ዑመር መዝገብ አራት ተጠርጣሪዎች ላይ የ14 ቀናት ተጨማሪ ጊዜ ተፈቀደ። አቶ አብዲ መሃመድ ዑመር፣ የሴቶችና ህጻናት ቢሮ የቀድሞ ኃላፊ ራህማ መሃመድ፣ የዲያስፖራ ጉዳዮች ጽህፈት ቤት የቀድሞ ኃላፊ አብዱራዛቅ ሳኒና የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር የነበሩት ፈርሃን ጣሂር በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አራተኛ ወንጀል ችሎት ቀርበዋል። መርማሪ ፖሊስ ከዚህ በፊት በተሰጠው የምርመራ ጊዜ የ20 ምስክር ቃል መቀበሉን፣ የአስከሬን ምርመራና የህክምና ማስረጃ፣ ከ740 ሚሊዮን ብር በላይ ጉዳት መድረሱን የሚያሳይ የሰነድ ማስረጃና የተለያዩ ሰነዶችን የማስተርጎም ስራዎች ማከናወኑን አብራርቷል። ''ከሐምሌ 26 እስከ 30 ቀን 2010 ዓ.ም 'ሄጎ' በሚል ስያሜ ህገ ወጥ ቡድን በማደራጀትና በማስታጠቅ በሰዎችና ሕይወት ላይና በኃይማኖት ተቋማት ንብረት ላይ ጉዳት የደረሰ በመሆኑና ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ በአራት ቦታዎች በጅምላ የተቀበሩ 200 ሰዎችን አስከሬን ምረመራ እያደረኩ ነው'' በሚል ምርመራው ተጨማሪ ጊዜ እንደሚጠይቅ አስረድቷል። በቀጣይም ተጨማሪ የሟች ቤተሰቦችና ተጎጂዎች የምስክር ቃል መቀበል፣ ያልተያዙ ግብረ አበሮችን በቁጥጥር ስር ማዋልና ተያያዥ ስራዎች እንደሚቀሩት ገልጾ የ14 ቀናት ተጨማሪ የጊዜ ቀጠሮ እንዲሰጠው ጠይቋል።   የተጠርጣሪ ጠበቆች በበኩላችው ''መርማሪ ያቀረበው ምክንያት ከዚህ በፊት ሲጠይቅ ከነበረው የተለየ ነገር የለውም፣ ተጠርጣሪዎች ከተያዙ አራት ወራት አልፏቸዋል፣ ያልተያዙ ግብረ አበሮችን መያዝ በሚል ምርመራው መዘግየት የለበትም፤ በአጠቃላይ ተጠርጣሪዎች የተፋጠነ ፍትህ የማግኘት መብታቸው እየተጣሰ ነው'' በማለት ተቃውመዋል። ግራ ቀኙን ያደመጠው ችሎቱ የምርመራ መዝገቡን ተመልክቶ ፖሊስ በርካታ ስራዎችን ማከናወኑን፣ ከቦታው ርቀትና አካባቢያዊ የጸጥታ ሁኔታ አንጻርና የወንጀል ድርጊቱን ውስብስብነት ግምት ውስጥ በማስገባት ተጨማሪ ጊዜ መፍቀድ እንደሚያስፈልግ ገልጿል። በዚህም መርማሪ ፖሊስ የጠየቀውን የ14 ቀናት በመፍቀድ ፖሊስ በፍጥነት ስራውን አጠናቆ የምርመራ ውጤቱን ይዞ እንዲቀርብ ለታኅሳስ 25 ቀን 2011 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም