የኢትዮጵያ እድገት አብዛኛውን ህብረተሰብ ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆን አንዳለበት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አሳሰበ

838

አዲስ አበባ ታህሳስ 10/2011 ኢትዮጵያ እያስመዘገበችው ያለው ፈጣን ምጣኔ ኃብታዊ እድገት አካታችና አብዛኛውን የህብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆን እንዳለበት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አሳሰበ።

በኢትዮጵያ ላለፉት ሁለት ቀናት ጉብኝት ያደረጉት የመንግስታቱ ድርጅት የልማት ፕሮግራም ዋና አስተዳዳሪ አቺም ስቴነር ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ ኢትዮጵያ በተለይ ካለፉት ጥቂት ዓመታት ጀምሮ ጠንካራ የሚባል አጠቃላይ አገራዊ እድገት እያመጣች መሆኑን ጠቅሰው ይህ እድገት ግን አብዛኛውን ዜጋ ተጠቃሚ የሚያደርግ ሊሆን ይገባል ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ በሚታየው የልማት ጎዳና እና በዚህ ዓመት የተጀመረው አጠቃላይ አገራዊ የለውጥ ሂደት አማካኝነት አገሪቱ በመጪዎቹ ጥቂት ዓመታት ውስጥ አብዛኛው ዜጋ ተጠቃሚ የሚሆንበትንና ዘላቂነት ያለውን የምጣኔ ኃብት የምታረጋግጥበት ይሆናል የሚል ተስፋ እንዳላቸው ዋና አስተዳዳሪው ገልፀዋል።

የልማት ፕሮግራሙ ላለፉት አራት አስርት ዓመታት የኢትዮጵያ የልማት አጋር ሆኖ ሲሰራ መቆየቱን የገለፁት ሚስተር ስቴነር ወደፊትም ይህንኑ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

አገሪቱ “ዘላቂ የልማት ግቦች” በሚል በመንግስታቱ ድርጅት የተቀየሰውን የልማት መርሃ ግብር ለማሳካት የበኩለሏን ጥረት እያደረገች መሆኑንም አስታውቀዋል።

አክለውም “የተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራምን ጨምሮ የተለያዩ የመንግስታቱ ድርጅት አካላት በዓለም አቀፉ የዘላቂ ልማት ግቦች አቅጣጫ መሰረት በኢትዮጵያ እየተንቀሳቀሱ ነው፤ የልማት ግቦቹ ኢትዮጵያ ከያዘቻቸው አገራዊ የልማት እቅዶችና የትኩረት አቅጣጫዎች  ጋር ከፍተኛ መጣጣም አላቸው፤ በመሆኑም በዚህ ረገድ የልማት ፕሮግራሙ የሚሰጠውን ድጋፍ ማጠናከር በሚችልበት መንገድ ላይ እንደገና እያሰበ ነው” ብለዋል።

የመንግስታቱ ድርጅት የልማት ፕሮግራም ዋና አስተዳዳሪ በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት የተጀመረውን ሁለንተናዊ የለውጥ ሂደት አድንቀዋል።

እየተካሄደ ያለው ለውጥ በተለይ በአፍሪካ ቀንድ ጠንካራ የምጣኔ ኃብት እድሎች እንዲፈጠሩ ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት የጀመረው ሁለንተናዊ የለውጥ ሂደት የሚፈለገው ደረጃን ይቀዳጅ ዘንድ የተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም  ተገቢውን ድጋፍ እንደሚያደርግም ቃል ገብተዋል።

የተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም ዋና አስተዳዳሪ በኢትዮጵያ ቆይታቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ አህመድን ጨምሮ ከሌሎች ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ጋር በጋራ ጉዳዮች ላይ መክረዋል።