ህጋዊ ነጋዴዎች ህገ ወጥ የቁም እንሰሳት ንግድ ስጋት እንደሆነባቸው ገለጹ

75
አዳማ ታህሳስ 10/2011 በህገ ወጥ መንገድ ወደ ጎረቤት ሀገራት የሚላኩ የቁም እንስሳት መስፋፋት ከገበያ ውድድር ውጪ ሊያደርጋቸው እንደሚችል በዘርፉ የተሰማሩ ህጋዊ ነጋዴዎች ስጋታቸውን ገለጹ። ከቁም እንስሳት ላኪዎች መካከል የአዳማ ከተማ ነዋሪው ሼህ ማህሙድ አህመድ ሁሴን ለኢዜአ እንዳሉት በየሶስት ወሩ ከ400 በላይ የቁም እንስሳት ወደ ተባባሩት  አረብ ኢሚሬትስ ፣ሳዑዲና ግብፅ ይልካሉ። ሆኖም ህገወጥ ነጋዴዎች በሀገር ውስጥ ገበያ የእንስሳት ዋጋ በማናርና በድብቅ ወደ ጎረቤት ሀገራት በመላክ  ህጋዊ ነጋዴዎች ከውድድር ውጪ ለማድረግ  በመንቀሳቀስ ስጋት እንደሆኑባቸው ተናግረዋል። "ከመጀመሪያ ደረጃ የግብይት ሰንስለት ጀምሮ ህገ ወጥ ደላሎች እጃቸውን ያስገቡበትና ሀብቱ በህገ ወጥ መንገድ ከሀገር ሲወጣ እያየን ነው" ብለዋል። ህጋዊ አሰራርን በመከተል ሰርተው  ራሳቸውን ብሎም ሀገራቸውን መጥቀም እንደሚፈልጉ ጠቅሰው ለዚህም   ከኳራንቲን ጣቢያዎች ግንባታና ጥራታቸውን ከማሻሻል ጀምሮ ጠንካራ የክትትልና ቁጥጥር ሥርዓት መዘርጋት እንደሚገባ  ጠቁመዋል። የደላሎች ሰንሰለት እጅጉን የገበያ ሥርዓቱ እንዲዛባና የእንስሳት ዋጋ ምክንያታዊ ባልሆነ መንገድ እንዲያሻቅብ እያደረገ መሆኑን  የገለፁት ደግሞ ሌላኛው በዚሁ ከተማ በዘርፉ የተሰማሩ ባለሃብት  አቶ አብዱልዋብ ደቀቦ ናቸው። "የሀገር ውስጥ የገበያ ዋጋ በደላሎች የበላይነት መያዙ በቁም እንስሳት ግብይት ላይ ከሚያጋጥሙን ችግሮች መካከል ቀዳሚው በመሆኑ መፍትሔ ሊፈለግለት ይገባል "ብለዋል ። በግብርና ሚኒስቴር የእንስሳት ሀብት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር  ገብረእግዚአብሔር ገብረዮሓንስ በአሁኑ ወቅት ሀብቱን ወደ መካከለኛው ምስራቅ ሀገራት እየተላከ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ሆኖም በሶማሊያ፣ፑንቲ ላንድ ፣ ሶማሊ ላንድ፣ጂቡቲና ኬንያ በኩል በየጊዜው በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ የኦጋዴንና ቦረና የቁም እንስሳት ዝሪያዎች እንደሚወጡ አመልክተዋል። መንግስት ችግሩን ለመፍታት የመጀመሪያ ደረጃ የገበያ ማዕከላትን ከማጠናከር ጀምሮ ሀብቱን በህገ ወጥ መንገድ ወደ ውጪ በማውጣት ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት  በሚንቀሳቀሱት ደላሎች ላይ እርምጃ ለመውሰድ እየተሰራ መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታው ተናግረዋል። "በዘርፉ ከሚስተዋለው ህገ ወጥ ንግድና የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ በተጨማሪ የሀገሪቱ የእንስሳት አረባብ፣አያያዝና እንክብካቤ አሰራር የምርቱን ተቀባይ ሀገራት ፍላጎት አያሟላም"  ያሉት ደግሞ በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የገበያ ጥናት ዳይሬክተር አቶ መኮንን ጋሹ ናቸው። በዚህም የአቅርቦት እጥረትና የጥራት ጉድለት በዘርፉ የሚታዩ ቁልፍ ችግሮች እንደሆኑ አመልክተዋል። ባለፈው ዓመት ወደ ውጭ ከተላኩት የቁም እንስሳት 60 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ መገኘቱን ጠቅሰው  ከእቅዱ አንፃር አፈፃፀሙ አነስተኛ መሆኑን ጠቁመዋል። ዳይሬክተሩ እንዳሉት በተያዘው የበጀት ዓመት ከዘርፉ  120 ሚሊዮን ዶላር ገቢ  ለማግኘት ታቅዶ እየተሰራ ነው፤ እቅዱ ሊሳካ የሚችለው በዘርፉ የሚስተዋለውን ህገ ወጥ ንግድና የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ መግታት ሲቻል ነው። የግብይ ሰንሰለትን ማዘመንና ተጠያቂነት የተለበሰ የአሰራር ሥርዓትን ለመዘርጋት፣ የመውጫ በሮች በተለይም አፋርና ሶማሌ ክልል፣ሞያሌና የሱዳን ድንበር አካባቢ የቁጥጥር ሥርዓት ማጠናከር  ላይ ከየክልሎቹ  ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል። የኦሮሚያ እንስሳትና ዓሣ ሀብት ልማት ኤጄንሲ ኃላፊ ዶክተር ከፈና ይፋ በበኩላቸው በዘርፉ የሚታየው ህገ ወጥነትን ለማስወገድ ስትራቴጅክ እቅድና የማስፈፀሚያ ስልት ተዘጋጅቶ ወደ ተግባር መገባቱን ገልጸዋል፡፡። "በሞያሌና በሱዳን በኩል ወደ ጎረቤት ሀገራት በርካታ የቁም እንስሳት እንዲወጡ በማድረግ በኩል ደላሎች የሚጫወቱት አፍራሽ ድርጊት ከፍተኛውን ድርሻ የያዘ መሆኑን በጥናት አረጋግጠናል "ብለዋል። ድርጊቱ  ሀገራዊ ኃላፊነት በማይሰማቸውና ራሳቸውን በአቋራጭ ለመበልፀግ በሚራራጡ አካላት የሚካሔድ በመሆኑ ቁጥጥሩን በማጠናከር በህግ ተጠያቂ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም