በኢትዮጵያ ያለው የንግድ ስርዓት ግልጽነት የጎደለው በመሆኑ ለኢኮኖሚ አሻጥር መንገድ ከፍቷል

190
አዲስ አበባ ታህሳስ 10/2011 በኢትዮጵያ ያለው የንግድ ስርዓት ግልጽነት የጎደለው በመሆኑ በተለያዩ ምርቶች ላይ አሻጥር እንዲፈጸም መንገድ የከፈተ መሆኑን የዘርፉ ምሁራን ገለጹ። የንግድ ውድድሩን ፍትሃዊና አስተማማኝ ለማድረግ ጠንካራ ተቋማትን መፍጠር እንደሚገባም አመልክተዋል። በአንድ አገር ላይ የኢኮኖሚ አሻጥር የሚፈጽሙ ቡድኖች ቁጥር እየጨመረ ሲመጣ የአገሪቱ ኢኮኖሚ የመውደቅ አደጋ እንደሚያጋጥመው ምሁራኑ ያስገነዝባሉ። በኢትዮጵያ በተለያዩ ምርቶች ላይ የሚፈጸሙ የኢኮኖሚ አሻጥሮች ምክንያታቸው ሰው ሰራሽ እጥረቶች እንደሆኑም ገልጸዋል። አሻጥር የሚፈጸምባቸው ምርቶች በተጠቃሚዎች ዘንድ ተፈላጊ በመሆናቸው በኢኮኖሚው ላይ የሚያሳድሩት ጫና ከፍተኛ ነው። ቡና፣ ቆዳ፣ ብረት፣ ነዳጅ፣ ስኳርና ዘይት የኢኮኖሚ አሻጥር ከሚፈጸምባቸው ምርቶች ውስጥ ተጠቃሽ ናቸው። ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ የዘርፉ ምሁራን እንደሚሉት፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የንግድ ስርዓት ግልጽነት የጎደለው በመሆኑ የኢኮኖሚ አሻጥር የሚፈጽሙ አካላት ቁጥር እየጨመረ መጥቷል። ኢትዮጵያ የነፃ ገበያ ስርዓት ኢኮኖሚ የምትከተል ቢሆንም ስርዓቱ ግልጽ በሆነ መንገድ የሚመራ ባለመሆኑ በተጠቃሚዎች ዘንድ ተፈላጊ በሆኑ ዕቃዎች ላይ የኢኮኖሚ አሻጥር እንደሚፈጸም ምሁራኑ አስረድተዋል። በዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሃብት ባለሙያ የሆኑት አቶ ብርሃኑ ያደቴ  በሰጡት አስተያየት   ''አሻጥር የሚሰራው አምራች  ወይም ሻጭ   የምርቶች ወይም ዕቃዎችን  ዋጋ ርካሽ ሲሆንበት  ያከማቻል  ግምቱ የሆነ ወቅት ዋጋ ይጨምራል የሚል ነው፤  ገበያው ላይ  የዕቃዎች ዋጋ በሚጨምርበት ጊዜ አውጥቶ ያልተገባ ትርፍ ለማግኘት  ያለመ ነው፤ እንደዚህ አይነት ሰዎች በአንድ ኢኮኖሚ ውስጥ በብዛት የሚገኙ ከሆነ የአገሪቷን ኢኮኖሚ  በከፍተኛ ደረጃ ይጎዳሉ ።'' ''መንግስትን ተጠግተው በማርኬቱ ላይ የራሳቸውን ጨዋታ የሚጫወቱ ተቋማት አሉ፤ እነዚህ ተቋማት ስርዓት የሚያግዳቸው ካልሆነና ግልጽነት የማይኖር ከሆነ ከመንግስት ጋር ያላቸውን ግንኙነት እንደ ዕድል በመጠቀም ዋጋ ይጨምራሉ ፤አቅርቦት ሲያጥር ዋጋ እንደሚጨምር ያውቃሉ፤  አርቴፊሽያል የሆነ እጥረት በመፍጠር ያላቸውን ምርት በውድ ዋጋ መሸጥ ይፈልጋሉ። በዚህ ሰዓት የኢኮኖሚ አሻጥር ይፈጠራል ማለት ነው'' የሚሉት ደሞ በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርስቲ የልማት ጥናት ባለሙያ ዶክተር ካሳ ተሻገር  ናቸው፡፡ ነጻ የገበያ ኢኮኖሚ በሚከተሉ አገሮች የገበያ ዋጋ የሚወሰነው በአቅርቦትና ፍላጎት ላይ ሲሆን የኢትዮጵያ የነፃ ገበያ ስርዓት ግልጽነት የጎደለውና የነፃ ገበያ ባህሪ የሌለው መሆኑን ምሁራኑ አስረድተዋል። በአሁኑ ወቅት ያለው የገበያ ስርዓት ጥቂት ነጋዴዎች በምርቶች ላይ ሰው ሰራሽ እጥረት በመፍጠር ገበያው እንዳይረጋጋ እንደሚያደርጉ አብራርተዋል። እንዲሁም የገበያ ስርዓቱ በጥቂቶች የተያዘ መሆን ነጋዴዎች በዋጋ ላይ ስምምነት በማድረግ በሁሉም የመሸጫ ቦታዎች በተመሳሳይ ዋጋ እንደሚሸጡ ያስረዱት ምሁራኑ ይህንን አሻጥር ለማስቀረት መንግስት የገበያ ስርዓቱ ግልጽነትን እንዲላበስ ማድረግ እንዳለበት ጠቁመዋል። በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርስቲ የልማት ጥናት ባለሙያ ዶክተር ካሳ ተሻገር በበኩላቸው''መንግስት የሚከተለውን የኢኮኖሚ ስርዓት በግልጽ ማስቀመጥ አለበት፤የምናውቀው ማርኬት ኢኮኖሚ ነው ፤በኢትዮጵያ ውስጥ  ግን የምንተገብረው ደግሞ ማርኬት ኢኮኖሚን አይደለም ሙሉ በሙሉ የመንግስት ጣልቃ ገብነት ከልክ ያለፈ በመሆኑ ማለት ነው ˝ ብለዋል። ˝ስለዚህ የመጀመሪያው ስራ መንግስት ሊከተለው ያሰበውን የኢኮኖሚ ስርዓት በይፋ ግልጽ ማድረግ አለበት፤ያ የኢኮኖሚ ስርዓት የሚፈልገውን ህግና ተቋም ደግሞ ማቋቋም አለበት፤ የተቋማት ጥንካሬ ይሄንን ይቆጣጠራሉ። ምን አይነት ፕሮዳክት እንዳለ የት እንዳለ ይታወቃል ስርዓት ሲኖር ማለት ነው ፤ስርዓት ሳይኖር ግን አሻጥሩ ይቀጥላል ˝  ብለዋል ዶክተር ካሳ፡፡ ''በአገሪቷ ላይ የዋጋ አለመረጋጋትን ሊፈጥሩ የሚችሉ ምርቶች አብዛኛው ከውጭ የሚመጡ ስለሆኑ አንድ ሰው ወደ ኢምፖርት ሲገባ የተቀመጡ መስፈርቶች በጣም ቀላል መሆን መቻል አለባቸው።ብዙ አስመጪዎች ብዙ ላኪዎች እንዲፈጠሩ ለማስቻል'' በማለት የተናገሩት በዩኒቨርስቲው የምጣኔ ሃብት ባለሙያ ነዚድ ናስር ናቸው፡፡ ''በኛ አገር ኢኮኖሚ ሰዎች በጤናማ መንገድ  ነግደው  ለማትረፍ  ሳይሆን አቋራጭ መንገዶችን ይጠቀማሉ ፤ያሉት የፋይናንስ ተቋሞች ተናበው የሚሰሩበት ማርኬት አይደለም።እነዚህ ተቋማት ከግለሰቦች ጋር እየተነጋገሩ የሚሰሩበት ሁኔታ አለ።መንግስትም ተከታትሎ አድኖ ለህግ የሚያቀርብበት ሁኔታዎች ብዙ አይታይም። ልቅ የሆነ ነገር ነው።  መኖሩን የምጣኔ ሃብት ባለሙያው አቶ ብርሃኑ አብራርተዋል፡፡ የአስመጪዎች ጥቂት መሆን፣ የግብይት ሰንሰለቱ መርዘምና ጠንካራ ተቆጣጣሪ አካል አለመኖር በኢትዮጵያ ውስጥ የኢኮኖሚ አሻጥር እንዲፈጸም የሚያደርጉ ምክንያቶች እንደሆኑም ገልጸዋል። መንግስት የገበያ ስርዓቱን ፍትሃዊና ተወዳዳሪ ለማድረግ የወጡ ህጎች፣ ደንቦችና መመሪያዎች በትክክል ተግባራዊ በማድረግ ገበያውን በየጊዜው ክትትል ሊያደርግበት እንደሚገባም ምሁራኑ ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም