በሜጀር ጀኔራል ክንፈ ዳኘው ላይ መርማሪ ፖሊስ የጠየቀው 14 ቀናት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ተፈቀደ

87
አዲስ አበባ ታህሳስ 10/2011 በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ፍርድ ቤት የቀረቡት ቀድሞው የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ዋና ዳይሬክተር ሜጀር ጀነራል ክንፈ ዳኘው ላይ ፖሊስ የጠየቀውን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ፍርድ ቤት ፈቀደ። አመልካች መርማሪ ፖሊስ ተጠርጣሪው ሜጀር ጀነራል ክንፈ ዳኘው ላይ ተጨማሪ የሙስና ወንጀል ድርጊት ማግኘቱን ከትናንት በስቲያ ለችሎቱ አመልክቶ ተጨማሪ የ14 ቀናት የምርመራ ጊዜ እንዲሰጠው ጠይቆ ነበር። ድርጅቱ የሚያከናውናቸውን ስምምነቶች 90 በመቶ በተጠርጣሪ የሚፈጸሙ መሆኑን በመግለጽ፣ ተጠርጣሪው ቢወጡ አጠቃላይ የምርመራውን ሂደት ያደናቅፋሉ በሚል የተጠርጣሪ ጠበቆች ያቀረቡትን ዋስትናም ተቃውሞ ነበር። ትናንት በተቀጠረው ክርክርም የተጠርጣሪ ጠበቆች መርማሪ ፖሊስ ያቀረበውን የተጨማሪ ምርመራ ጊዜ ተቃውመዋል። በተጠርጣሪው ላይ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ለመፍቀድ ወይም ዋስትና ለመፍቀድ ለዛሬ በይደር ቀጥሮ የነበረው ፍርድ ቤቱ ፖሊስ ተጨማሪ ምርመራ አድርጎ ለታህሳስ 22 ቀን 2011 ዓ.ም ጊዜ ቀጠሮ ሰጥቷል። መርማሪ ፖሊስ አዳዲስ የምርመራ ግኝቶችን ጨምሮ በአጠቃለይ በ18 የሙስና ወንጀል ድርጊቶች ተሳትፎዎችን ይፋ አድርጎ ነበር። በነዚህና በሌሎች በአጠቃላይ በ18 የሙስና ወንጀል ድርጊቶች የሰነድ ማስረጃዎችን ለማሰባሰብ፣ ምስክሮችን ቃል ለመቀበልና ሌሎች አስፈላጊ ምርመራዎችን ለማድረግ የ14 ቀናት ተፈቅዶለታል። በተያያዘ ፍርድ ቤቱ በዛሬው ችሎት በሰብዓዊ መብት ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የሚገኙት የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ባልደረባ የነበሩት አቶ ማርክስ ፀሐይ ላይ ፖሊስ የተጎጂ ቃል መቀበል፣ የህክምና ማስረጃ ማሰባሰብ፣ የተጎጂ ንብረት ጉዳት ማስገመትና ከአዲስ አበባ ውጪ የሄዱ የምርመራ አባላት ውጤት እንደሚጠብቅ ገልጾ 14 ቀናት የምርመራ ጊዜ እንዲሰጠው በጠየቀው መሰረት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ተፈቅዶለታል። በመሆኑም ለታህሳስ 22 ቀን 2011 ዓ.ም እንዲቀርብ ታዟል። በሰብዓዊ መብት ጥሰትና ሙስና ወንጀል ተጠርጣሪ ተስፋዬ ዑርጌ ላይ ፖሊስ የጠየቀው ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ተፈቅዶ በተመሳሳይ ለታህሳስ 22 ቀን 2011 ዓ.ም እንዲቀርብ ትዕዛዝ ሰጥቷል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም