ሴቶች አገራዊ ሰላምን የሚያውኩ አፍራሽ ተግባራትን ለመቀየር ቁልፍ ሚና ሊጫወቱ ይገባል ተባለ

76
አዲስ አበባ  ታህሳስ 10/2011 የኢትዮጵያ ሴቶች የተጀመረውን አገራዊ ለውጥ የሚያደናቅፉና ሰላሙን የሚያውኩ አፍራሽ ተግባራትን ለመቀየር በተደራጀ መንገድ መስራት እንዳለባቸው የኢህዴግ ሴቶች ሊግ አሳሰበ። ሴቶች በአገሪቱ አስተማማኝ ሰላም ይረጋገጥ ዘንድ የዜጎችን አስተሳሰብ የሚቀይሩ ሥራዎች ላይ እንዲተጉም ሊጉ ጠይቋል። በመቀለ ከተማ ለሶስት ቀናት ሲካሄድ የቆየው 4ኛው የኢህአዴግ ሴቶች ሊግ ጉባኤ የሴቶች ተጠቃሚነት የሚረጋገጠው አገራዊ ሰላም ሲረጋገጥ በመሆኑ ሴቶች ለሰላም መስፈን ሚናቸውን እንደሚወጡ ቃል በመግባት ነው ትላንት የተጠናቀቀው። ሊጉን እንዲመሩ  በሊቀመንበርነት የተመረጡት ወይዘሮ መሰረት መስቀሌ የተጣለባቸውን ኃላፊነት በብቃት ለመወጣት እንደሚሰሩ ተናግረዋል። አዲሷ ሊቀመንበር ከተመረጡ በኋላ በተለይም ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት ሴቶች የተጀመረውን አገራዊ ለውጥ የሚያደናቅፉ እና ሰላሙን የሚያውኩ አፍራሽ ተግባራትን በተደራጀ መንገድ መታገል አለባቸው ብለዋል። ወይዘሮ መሰረት፤ የተጀመረውን አገራዊ የለውጥ ሂደት ከዳር ለማድረስ እና የተዛቡ አመለካከቶችን ለመቀየር የሚያስችሉ ተግባራት እንደሚከናወኑም ገልፀዋል። የኢህዴግ ሴቶች ሊግም አገራዊ አንድነት የሚያጠናክሩ ሥራዎች ላይ በትኩረት እንደሚሰራ ነው የገለፁት።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም