በርካታ ዓለም አቀፍ አየር መንገዶች በሱማሊያ በረራ ለመጀመር ይፈልጋሉ

160
ታህሳስ 10/2011 የአገሪቱ አጠቃላይ ጸጥታና የሞቃዲሾ አየር መንገድ ደህንነት ከግዜ ወደ ግዜ  መሻሻሉ የተለያዩ አለም አቀፍ አየር መንገዶች ወደ  ሱማሊያ ሞቃዲሾ ይፋዊ በረራ ለማድረግ ፍላጎት እያሳደረባቸው እንደሚገኝ ተገለጸ፡፡ ኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ሞቃዲሾ በረራ መጀመሩ ይታወቃል፡፡ በሞቃዲሾ አለም አቀፍ አየር መንገድ  የአለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክተር ሰይድ ኤሊያ እንደተናገረው የሱማሊያ  ጸጥታ መሻሻል  የተለያዩ የአለም አቀፍ አየር መንገዶች በረራ ለመጀመር መተማመን ፈጥሮላቸዋል ፡፡ በረራ ለመጀመር ከአገሪቱ አየር መንገድ ጋር በረራውን በሚጀምሩበት ሁኔታ ላይ ውይይት እያደረጉ እንደሆነ ዳሬክተሩ ጨምሮ  አስታውቋል፡፡ እንደ ዳሬክተሩ ገለጻ የአገሪቱ ጸጥታ መሻሻልን ተከትሎ  የኬኒያ አየር መንገድ ከናይሮቢ  ወደ ሞቃዲሾ የቀጥታ በረራ  ከዛሬ ጀምሮ በይፋ መጀመሩንም  ዳሬክተሩ ተናግረዋል፡፡ በረራ መጀመሩን ተከትሎ 3ኛው ወደ ሞቃዲሾ አለም አቀፍ በረራ የጀመረ  አየር መንገድ መሆንም ችሎል፡፡ የቱርክ አየር መንገድና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ሞቃዲሾ ቀድመው በረራ ማድረግ የጀመሩ አየር መንገዶች መሆናቸው ይታወቃል፡፡ በሌላ በኩል የኳታር አየር መንገድ በቅርቡ ወደ ሞቃዲሾ በረራ ለማድረግ ዝግጅት እያደረገ ሲሆን የግብጽ የተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ  ሳውዳአረቢያ እና የዩጋንዳ አየር መንገዶች በረራ ለማድረግ ፍላጎታቸውን የገለጹ  መሆናቸውን የሲጂቲኤን ዘገባ ያመለክታል፡፡ አሚሶም እያደረገ ባለው ድጋፍ የአገሪቱ የጸጥታ ሁኔታ በከፍተኛ ሁኔታ መሻሻሉን የተናገሩት  ዳይሬክተሩ አየር መንገዱም  በቀጣይ ደህንነቱ የተጠበቀ  አስተማማኝ አየር መንገድ ለመሆን  በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ ተናግሯል፡፡ አየር መንገዱ ከአሚሶም ጋር ጥምረት በመፍጠር ለሰላም ጉዳይ ከምንም በላይ ቅድሚያ በመስጠት ደህንነትና የጸጥታ ጉዳይ ላይ በጋራ ይሰራል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም