ተቋማት በቀድሞ ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ ህልፈተ ህይወት የተሰማቸውን ሐዘን ገለጹ

60
አዲስ አበባ ታህሳስ 9/2011 የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት ኤጀንሲ እና የአበበች ጎበና የሕፃናት ክብካቤና ልማት ማህበር በቀድሞ ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ ህልፈተ ህይወት የተሰማቸውን ሐዘን ገለጹ። የብሔራዊ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት ኤጀንሲ ለኢዜአ በላከው መግለጫ ፕሬዝዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ የንባብ ባህል እንዲያድግ መጽሕፍት በማሰባሰብና በማደራጀት ዲጂታል ቤተ መጻሕፍት በማቋቋም እና ለአንባቢያን ክፍት በማድረግ ለኤጀንሲው እገዛ ያደረጉ መሪ ነበሩ። ህዳር 28 ቀን 1995 የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት ኤጀንሲ ሕንፃ ግንባታ መሠረት ድንጋይ የጣሉና በኤጀንሲው የንባብ ባህል እንዲያድግ አስተዋጽኦ አበርክተዋል። ኤጀንሲው በህልፈታቸው የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን በመግለጽ ለቤተሰቦቻቸው መፅናናትን ተመኝቷል። በተመሳሳይ የአበበች ጎበና የሕፃናት ክብካቤና ልማት ማህበር በፕሬዚዳንቱ ሞት የተሰማውን ሐዘን ገልጾ ለቤተሰቦቻቸውና ለኢትዮጵያ ህዝብ  መፅናናትን ተመኝቷል። መቶ አለቃ ግርማ ወልደጊዮርጊስ ከ1994 እስከ 2006 ዓም የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት በመሆን ያገለገሉት ሲሆን በተወለዱ በ95 ዓመታቸው ታህሳስ 5 ቀን 2011 ዓ.ም  ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም