የአካል ጉዳተኞች ችግርን ለመፍታት ገና ብዙ መስራት ይጠይቃል---የጉዳዩ ባለቤቶች

86
አዳማ ታህሳስ 9/2011 የአካል ጉዳተኞች በጤና፣ በትምህርትና በስራ ስምሪት ዘርፍ የሚያጋጥሙዋቸው ችግሮች ለመፍታት መልካም ጅምሮች ቢኖሩም ገና ብዙ መስራት የሚጠይቅ መሆኑን የጉዳዩ ባለቤቶች ገለጹ። ወጣት ዘነበች ጌታነህ የአካል ጉዳተኛ ስትሆን ሁሉንም ስራዎቿ የምታከናውነው በዊልቸር እየታገዘች ነው። የጤናና የትምህርት አገልግሎት ለማግኘት የሚሄዱ የአካል ጉዳተኞች አመቺ መንገድ ስላልተዘጋጀላቸው ወደ ውስጥ ለመግባት እንኳን እንደሚቸገሩ ለኢዜአ  ተናግራለች። ወጣት ዘነበች እንዳለችው ወደ ጤና ተቋማት እንደምንም ተቸግረው ቢገቡ እንኳን አመቺ መፀዳጃ ቤቶች ስላልተዘጋጁላቸው ለቤተ ሙከራ  ምርመራ የሚያስፈልጉ ናሙና ለማምጣት ይቸገራሉ። እቤት ድረስ ሔደውና መፀዳጃ ቤት ተጠቅመው የታዘዙትን በ30 ደቂቃዎች ውስጥ ለማድረስ ያለው ግብግብ እልህ አስጨራሽ እንደሆነም ገልጻለች፡፡ "በተለይ ደግሞ አገልግሎቱን ፍለጋ ወደ ተቋማቱ የሚሄዱ መስማት የተሳናቸው ወገኖች ከአገልግሎት ሰጪዎቹ ጋር መግባባት ስለማይችሉ በህክምናውም ሆነ በትምህርቱ መስክ ሰፊ ክፍተት አለ" ብላለች። እነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች የአገልግሎቱ ፍትሃዊ ተጠቃሚዎች ለማድረግ አገልግሎት ሰጪ ተቋማቱ የምልክት ቋንቋ ባለሙያዎች እንደሚያፈልጋቸው ተናግራለች። "የስራ ማስታወቂያዎችም ቢሆኑ አካል ጉዳተኞችን ጭምር ታሳቢ ያደረጉ መሆን አለባቸው" ያለችው ወጣት ዘነበች አካል ጉዳተኞች ዊልቸር ላይ ተቀምጠው የሚያነቡበት፣ ዓይነ ስውራን  ደግሞ በብሬል እየታገዙ መረጃው የሚያገኙበት አማራጭ ሊፈጠር እንደሚገባም ጠቅሳለች። መልካም ጅምሮች እንዳሉ ገልጻ ከችግሩ ስፋት አንፃር በተለየ ትኩረት እንዲሰራበትም አሳስባለች። በአካል ጉዳተኞች ብሔራዊ ማህበራት ፌዴሬሽን የፕሮጀክት አስተባባሪ ወይዘሮ ስምረት ዘነበ በበኩላቸው የአካል ጉዳተኞች ጉዳይ ከ17 ሚሊዮን በላይ ስለሆኑ ወገኖች መሆኑን አስረድተዋል። በጤናው ፣ በትምህርትና በስራ ስምሪት ጉዳይ ያሉ ችግሮች ደረጃ በደረጃ ለመፍታት ቀዳሚው ተግባር የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ መሆን እንዳለበት ጠቁመዋል። "የህብረተሰቡ ግንዛቤ ካደገ ችግሮቹን የመፍታት ጉዳይም የራሱ የህብረተሰቡ ይሆናል "ብለዋል ። የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ግን የተነሱ ችግሮችን ለመፍታት የአካል ጉዳተኞች አካታች መመሪያ ጭምር በማዘጋጀት ወደ ተግባር መግባቱን አመልክተዋል። በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የሴቶችና ወጣቶች ጉዳይ ዳይሬክቶሬት የጥናትና ስልጠና ባለሙያ አቶ አቤል ሙሴ እንዳሉት የአካል ጉዳተኞች ተጠቃሚነት በጤናው ዘርፍ በማካተትና ተቋማዊ በማድረግ ጥራትና ፍትሀዊነት ያለው አገልግሎት ለመስጠት እየተሰራ ነው። "ጤናና ጤና ነክ መረጃዎች በምልክት ቋንቋ ፣ በብሬል ፣ በሬዲዮና ቴሌቪዥን ተደራሽ የማድረግ ስራ እየተካሔደ ነው "ብለዋል። የአካል ጉዳተኞች ማካተቻ መመሪያ ተዘጋጅቶ በ3ሺህ 500 የአማርኛና እንግሊዝኛ ኮፒ ታትሞ መሰራጨቱን ጠቅሰው ስልጠናዎች መሰጠታቸውንና ተገቢውን በጀት ተመድቦ ወደ ስራ መገባቱን አስረድተዋል። ባለፉት አምስት ዓመታት በተለያዩ የጤና ተቋማት ለ723 አገልግሎት ሰጪዎች፣ የጥበቃ ሰራተኞችና ለአስተዳደር ሰራተኞች የምልክት ቋንቋ ስልጠና መሰጠቱንም ባለሙያው አስታውሰዋል። የምልክት ቋንቋ መዝገበ ቃላት ተገዝተውም በየጤና ተቋማቱ እንዲቀመጡ መደረጉን ያመለከቱት አቶ አቤል "ከአጠቃላይ የሀገራችን ህዝብ 17 ነጥብ 6 በመቶ የሚሆኑት አካል ጉዳተኞች ናቸው"ተብለዋል። እነዚህ ወገኖች በተያዘው  ወር መግቢያ ዓለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞች ቀን ያከበሩ ሲሆን የዚሁ ቀጣይ የሆነ የሶስት ቀናት ዓውደ ጥናት ዛሬ በአዳማ ከተማ ተጀምሯል። ዓላማውም የአካል ጉዳተኞች በጤና ፣ በትምህርት ዘርፍና በስራ ስምሪት ላይ  በሚያጋጥሙዋቸው ቸግሮች ዙሪያ በመምከር የመፍትሔ ሃሳቦች ለማመንጨት ነው። የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ፣ የመንግስታዊ ተቋማት ተወካዮች ፣ የሚመለከታቸው ማህበራትና ድርጅቶች በአውደ ጥናቱ እየሳተፉ ነው፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም