ፍርድ ቤቱ በሙስና ወንጀል በተጠረጠሩት አቶ ኢሳያስ ላይ 10 ቀናት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ፈቀደ

422

አዲስ አበባ ታህሳስ 9/2011 ፍርድ ቤቱ በሙስና ወንጀል በተጠረጠሩት አቶ ኢሳያስ ዳኘው ላይ 10 ቀናት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ፈቀደ።

አመልካች የፌዴራሉ ወንጀል ምርመራ ቢሮ በተጠርጣሪው ላይ ተጨማሪ 14 ቀናት የጊዜ ቀጠሮ ጠይቆ የነበረ ሲሆን የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ከታህሳስ 4 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ የሚታሰብ የ10 ቀናት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ በመፍቀድ ለታህሳስ 15 ቀን 2011 ዓ.ም ፖሊስ ምርመራውን አጠናቆ እንዲቀርብ አዟል።

በተጠርጣሪነት የቀረቡት አቶ ኢሳያስ ዳኘው የኢትዮ­ ቴሌኮም የስራ ኃላፊ በነበሩበት ወቅት ድርጅታቸው በሶማሌ ክልል የሞባይል ተደራሽነትን ለማስፋት የሞባይል ሲ ዲ ኤም ስራዎችን ለማከናወን የብረታ ብረት ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ጋር የገባውን የውል ስምምነት ማሻሻያ በማድረግ በሌላቸው ኃላፊነት ሙሉ ክፍያ እንዲፈጽም በማድረግ ወንጀል ፖሊስ ጠርጥሯቸዋል።

በውሉ መሰረትም 201 ሚሊዮን ብር የነበረውን ውል ተጨማሪ ሳይት ለመገንባት በሚል ወደ 322 ሚሊዮን ብር ክፍያ እንዲፈም ለፋይናንስ ክፍል ደብዳቤ ጽፈዋል ብሏል።

ተጠርጣሪው ትናንት በችሎቱ ቀርበው በነበሩበት ወቅት ኢትዮ ቴሌኮም ሥራውን ካለምንም ጨረታ ለሜቴክ ቢሰጥም ሜቴክ ግን ለ17 ንዑስ ተቋራጮች በመስጠት ጥራት በጎደለው ሁኔታ እንዲሰራ፣ የተከናወነው ሥራም 91 ነጥብ 8 በመቶ ቢሆንም ሙሉ ክፍያው መፈጸሙን አስረድቷል።

የተጠርጣሪው ጠበቆች በበኩላቸው በተቋማቱ መካከል ስምምነቱ በተደገበት ወቅት በሶማሌ ክልል በነበረው የጸጥታ ችግር ምክንያት ሌሎች ተቋራጮች እንዳይገቡ ተደርጎ በቦርድ ውሳኔ ለሜቴክ የተሰጠ በመሆኑ ተጠርጣሪን አይመለከትም ብለዋል።

ለዚህ ደግሞ ተጠረጣሪው አስፈላጊውን ማስረጃ መስጠት እንደሚችሉ፣ መርማሪ ፖሊስ ምርመራውን በትጋት ባለመስራቱ እንጂ ተጠርጣሪውን ለ35 ቀናት በእስር ሊያስቆይ የሚችል ምክንያት እንደሌለ በመግለፅ ተከራክረዋል።

ተጠርጣሪው የዋስትና መብታቸው ተከብሮ በውጭ ሆነው እንዲከራከሩም ጠበቆቹ ጠይቀዋል።

የግራ ቀኙን ክርክር ያደመጠው አስረኛው ወንጀል ችሎት በተጠየቀው የተጨማሪ ጊዜና ዋስትና ጥያቄ ላይ ለመወሰን ለዛሬ ከሰዓት ቀጠሮ በሰጠው መሰረት ግራ ቀኙ ባደረጉት ክርክር መሰረት ለፖሊስ 10 ተጨማሪ የምርመራ ቀናት ፈቅዷል።