በኢትዮ-ጅቡቲ ምድር ባቡር መስመር በእንስሳት ላይ የሚደርሰው ግጭት መቀነሱ ተገለፀ

117
አዲስ አበባ ታህሳስ  9/2011 በኢትዮ-ጅቡቲ የምድር ባቡር መስመር ላይ በየጊዜው በእንስሳት ላይ የሚደርሰው ግጭት አደጋ በአሁኑ ወቅት እየቀነሰ መምጣቱ ተገለፀ። አደጋው ሊቀንስ የቻለው በአካባቢው ያለው ማህበረሰብ ለአደጋ ተጋላጭ እንዳይሆን ከወር በፊት የተጀመረውን የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሃ ግብር ተከትሎ መሆኑን ድርጅቱ አስታውቋል። ሥራ ከጀመረ ገና አንደኛ ዓመቱን እየደፈነ ያለው የኢትዮ-ጅቡቲ ምድር ባቡር የተገነባው ከ4 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ነው። ድርጅቱ አገልግሎት መስጠት ከጀመረበት ከዚህ ጊዜ አንስቶ በደረሰው የእንስሳት ግጭት አደጋ ሳቢያ  እስከ 4.5 ሚሊዮን ብር የሚደርስ ካሳ በመክፈል ለኪሳራ ተዳርጓል። በተለይ አደጋው ከአዳማ እስከ መኤሶ ባለው የባቡር መስመር ላይ የከፋ መሆኑን የኢትዮ ጅቡቲ ባቡር ትራንስፖርት አክሲዮን ማህበር ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ጥላሁን ሳርካ ለኢዜአ ገልፀዋል። አደጋውን ለመቀነስ በየጊዜው በአካባቢው ካሉ የኀብረተሰብ ክፍሎች ጋር ውይይት መደረጉን ዋና ዳይሬክተሩ ገልፀው በዚህም የሚደርሰውን አደጋ መቀነስ መቻሉን ነው ያብራሩት። በተያዘው ዓመት ጥቅምት ወር በደረሰ አደጋ 23 ግመሎች ሞተዋል፤ በመስመሩ ላይ የነበረው ባቡርም ለአንድ ቀን ታግቶ ካለስራ መቆሙን አውስተዋል። ባለፈው ህዳር ወር ተግባራዊ የሆነውን ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሃ ግብር ተከትሎ ግን የተመዘገበው የግጭት አደጋ የአራት ፍየሎች ብቻ መሆኑን አመልክተዋል። ከግንዛቤ ማስጨበጫ መርሃ ግብሩ በተጨማሪ በባቡር መስመሩ ማቋረጫዎች ላይ ሰራተኞች በመመደብ የትራፊክ ስራ አመራር ተግባር መጀመሩም አደጋው እንዲቀንስ እያደረገ ነው ብለዋል። በቀጣይም ማቋረጫዎችን የማጠር ስራ ይከናወናል ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ  አደጋውን ለመቀነስ የተጀመሩ ስራዎችም ተጠናክረው ይቀጥላሉ ሲሉም ተናግረዋል። የኢትዮ-ጅቡቲ ምደር ባቡር ትራንስፖርት አክሲዮን ማህበር ሰውና እቃ በማጓጓዝ እስከተያዘው ወር መጨረሻ ድረስ ግማሽ ቢሊዮን ብር ትርፍ ለማግኘት አቅዶ እየሰራ ነው። የተያዘው ይህ እቅድ ይሳካል የሚል እምነት እንዳላቸው ዋና ዳይሬክተሩ ኢንጂኒየር ጥላሁን ለኢዜአ ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም