በሰሜን ሸዋ ዞን በዚህ ዓመት ከ15 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ በኩታ ገጠም መስኖ ይለማል

69
ደብረብርሃን 9/2011 በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ስድስት ወረዳዎች በዚህ ዓመት ከ15 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ በኩታ ገጠም መስኖ እንደሚለማ የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ። ኩታ ገጠም ልማት ለአርሶ አደሩ ግብዓቶችን ለማቅረብና የባለሙያ ድጋፍ ለመስጠት አስችሏል። በመምሪያው አትክልትና ፍራፍሬ መስኖ ውሃ አጠቃቀም ቡድን መሪ ወይዘሮ አስካለ ይፍሩ እንደገለጹት በወረዳዎቹ 32 ሺህ የሚጠጉ አርሶ አደሮችን በማሳተፍ 3 ነጥብ 4 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት ታቅዷል፡፡ ልማቱ አርሶ  አደሩ በበጋ ወቅት አትክልትና ፍራፍሬ፣ ጥራጥሬ፣አዝርዕት፣ቅመማ ቅመምና የሥራሥር ሰብሎችን እስከ ሦስት ጊዜ ለማልማት ያስችለዋል ብለዋል፡፡ ልማቱ የክረምት ዝናብ ውሃን በማቆር፣ወራጅ ወንዞችን በመጥለፍና ምንጮችን በማጎልበት እንደሚከናወንም አስረድተዋል፡፡ እስካሁንም ሦስት ሺህ ሄክታር መሬት መልማቱን ወይዘሮ አስካለ ገልጸዋል፡፡ በአንጾኪያ ገምዛ ወረዳ የኩሬየጎደል ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ትዕዛዙ ምንዳዬ እንደገለጹት አንድ ሄክታር መሬት በኩታ ገጠም ሽንኩርት፣ ቲማቲምና ድንች ያለማሉ። በዚህም ምርታቸው በዱር እንስሳትና በተባይ በቀላሉ እንዳይጠቃ ከማድረጉም በላይ፤ የተለያዩ ግብዓቶችን በአንድ ላይ ለመጠቀም እንዳስቻላቸው ተናግረዋል። ልማቱ ወንዞችን በመጥለፍና በደቦ በማከናወን በዓመት ሦስት ጊዜ በማምረት 120 ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት አቅጄያለሁ ብለዋል፡፡ አምና ግማሽ ሄክታር መሬት አልምተው 50 ኩንታል ምርት ማግኘታቸውን አስታውሰዋል። በዚሁ ወረዳ የአጥቆ ቀበሌ ነዋሪ ወጣት አርሶ አደር ታደሰ በላይነህ በግማሽ ሄክታር መሬት ላይ ከ80 ኩንታል በላይ ሽንኩርት፣ቲማቲምና ካሮት ለማግኘት በመሥራት ላይ እንደሚገኝ ተናግሯል፡፡ በዞኑ ዘንድሮ በመስኖ ከሚለማው 96 ሺህ ሄክታር መሬት ከ14 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም