ፍርድ ቤቱ የሜጀር ጀኔራል ክንፈ ዳኛውንና የወንድማቸው ኢሳያስ ዳኘውን የችሎት ውሎ ለነገ ተቀጠረ

51
አዲስ አበባ ታህሳስ 8/2011 ፍርድ ቤቱ በሙስና ወንጀል ተጠርጣሪዎች የሜጀር ጀኔራል ክንፈ ዳኘውንና የወንድማቸው ኢሳያስ ዳኘውን ጉዳይ ለነገ ቀጠረ። አመልካች የፌዴራሉ ወንጀል ምርመራ ቢሮ በተጠርጣሪዎች ላይ የተጨማሪ 14 ቀናት የጊዜ ቀጠሮ ጠይቋል። መርማሪ ፖሊስ ሜጀር ጀኔራል ክንፈ ዳኘው ጉዳይን በሚመለከት 18 የወንጀል ድርጊቶች ያከናወናቸውንና ቀረኝ የሚለውን ለችሎቱ አመልክቷል። ነገር ግን ከጉዳዩ ስፋት አኳያ በተጠርጣሪው ላይ የዋስትናና የተጨማሪ ጊዜ ምርመራ ላይ በተጠርጣሪ ጠበቃና በአመልካች መካከል ክርክር ለማድረግ የችሎት ሰዓት በማለቁ ችሎቱ ክርክሩን ሰምቶ ለመወሰን ለነገ ከሰዓት ለአዳር ቀጥሯል። በተመሳሳይ መዝገብ በሁለተኛ ተጠርጣሪነት የቀረቡት አቶ ኢሳያስ ዳኘው የኢትዮ­ ቴሌኮም የስራ ኃላፊ በነበሩበት ወቅት ድርጅታቸው በሶማሌ ክልል የሞባይል ተደራሽነትን ለማስፋት የሞባይል ሲ ዲ ኤም ስራዎችን ለማከናወን ከሜቴክ ጋር የገባውን የውል ስምምነት ማሻሻያ በማድረግ በሌላቸው ኃላፊነት ሙሉ ክፍያ እንዲፈጽም አድርገዋል ብሏል ፖሊስ። በውሉ መሰረትም 201 ሚሊየን ብር የነበረውን ውል ተጨማሪ ሳይት ለመገንባት በሚል ወደ 322 ሚሊየን ብር ክፍያ እንዲፈም ለፋይናስ ክፍል ደብዳቤ ጽፈዋል ብሏል። ኢትዮ ቴሌኮም ሥራውን ካለምንም ጨረታ ለሜቴክ ቢሰጥም ሜቴክ ግን ለ17 ንዑስ ተቋራጮች በመስጠት ጥራት በጎደለው ሁኔታ እንዲሰራ፣ የተከናወነው ሥራም 91 ነጥብ 8 በመቶ ቢሆንም ሙሉ ክፍያው መፈጸሙን አስረድቷል። የተጠርጣሪው ጠበቆች በበኩላቸው በተቋማቱ መካከል ስምምነቱ በተደረገበት ወቅት በሶማሌ ክልል በነበረው የጸጥታ ችግር ምክንያት ሌሎች ተቋራጮች እንዳይገቡ ተደርጎ በቦርድ ውሳኔ ለሜቴክ የተሰጠ በመሆኑ ተጠርጣሪን አይመለከትም ብለዋል። ለዚህ ደግሞ ተጠረጣሪው አስፈላጊውን ማስረጃ መስጠት እንደሚችሉ፣ መርማሪ ፖሊስ ምርመራውን በትጋት ባለመስራቱ እንጂ ተጠርጣሪውን ለ35 ቀናት በእስር ሊያስቆይ የሚችል ምክንያት እንደሌለ በመግለፅ ተከራክረዋል። ተጠርጣሪው የዋስትና መብታቸው ተከብሮ በውጭ ሆነው እንዲከራከሩም ጠበቆቹ ጠይቀዋል። የግራ ቀኙን ክርክር ያደመጠው አስረኛው ወንጀል ችሎት በተጠየቀው የተጨማሪ ጊዜና ዋስትና ጥያቄ ላይ ለመወሰን ለነገ ከሰዓት ቀጠሮ ሰጥቷል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም