የጊዳቦ መስኖ ግድብ ፕሮጀክት ተጠናቆ በተያዘው ወር መጨረሻ ርክክብ ይካሄዳል

75
አዲስ አበባ  ታህሳስ 8/2011 በ2002 ዓ.ም ግንባታው የተጀመረው የጊዳቦ መስኖ ፕሮጀክት ተጠናቆ በተያዘው ወር መጨረሻ ላይ ርክክብ እንደሚካሄድ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን አስታወቀ። የጊዳቦ መስኖ ፕሮጀክት በደቡብ ብሔሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦችና በኦሮሚያ ክልሎች የሚገኙ 26 ሺህ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ለማድረግ ታስቦ በ910 ሚሊዮን ብር ወጪ ግንባታው መካሄድ የጀመረው። የጊዳቦ መስኖ ግድብ 63 ሚሊዮን ሜትር ኩብ ውኃ የሚይዝና 11 ሺ ሄክታር መሬት የማልማት አቅም አለው። የኮርፖሬሽኑ የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ስራ አስኪያጅ አቶ ጥንፉ ሙጬ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የጊዳቦ መስኖ ግድብን ጨምሮ ኮርፖሬሽኑ ከሚያካሂዳቸው 15 የግንባታ ፕሮጀክቶች መካከል አብዛኞቹ በተያዘው ዓመት ይጠናቀቃሉ ተብሎ ይጠበቃል። በዚህ ዓመት የርብ ግድብን አጠናቆ ያስረከበው ኮርፖሬሽኑ የመስኖ ግድቦች ግንባታ አፈጻጸሙ የተሻለ እንደሆነ አቶ ጥንፉ አስረድተዋል። ኮርፖሬሽኑ የተጓተቱ ፕሮጀክቶች እንዳሉት የተናገሩት አቶ ጥንፉ ከወሰን ማስከበር ጋር በተያያዘ የዘገዩ ፕሮጀክቶች መኖራቸውንም ገልጸዋል። የአርጆ ዴዴሳ ስኳር ፋብሪካ የመስኖ ስራ፣ የወልቃይት ስኳር ልማት መስኖ ስራ እና የቦሌ ቡልቡላ ጥልቅ ውሃ ጉድጓድ የውኃ ቦይ መስመር ግንባታ የዘገዩ ፕሮጀክቶች መሆናቸውን ጠቁመዋል።  የመስኖ ግድቦች መገንባት ብቻውን በቂ አለመሆኑን የገለጹት አቶ ጥንፉ "የግድቦቹ የውኃ ቦይ ግንባታ ተጠናቆ ወደ ልማት መግባት አለባቸው" ብለዋል። የርብ ግድብ 230 ሚሊዮን ሜትሪክ ኪዩብ ውኃ የመያዝና 14 ሺ ሄክታር መሬት የማልማት አቅም ቢኖረውም የውኃ ቦይ ግንባታ ባለመከናወኑ ግድቡ አገልግሎት መስጠት እንዳልቻለ አመልክተዋል። ግድቡን ለአገልግሎት ለማብቃት የሚያስችል ተግባራት መከናወን እንዳለበትም አስገንዝበዋል። በኢትዮጵያ የግብርው ዘርፍ ለአጠቃላይ ኢኮኖሚው ዕድገት ትልቅ ሚና ያለው ቢሆንም ሚናውን በአግባቡ እየተወጣ እንዳልሆነም የምጣኔ ኃብት ባለሙያዎች ይገልፃሉ። በመሆኑም ዘርፉ የሚገባውን ሚና እንዲጫወት ዘመናዊ አሰራርን ከመዘርጋት ባሻገር የመስኖ ልማትን በእጅጉ ማስፋፋት ወሳኝ እንደሆነም ይመክራሉ። ሆኖም ግን በአገሪቷ የተጀመሩ የተለያዩ የመስኖ ግድብ ግንባታዎች በተያዘላቸው ጊዜ ተጠናቀው ወደ ሥራ እየገቡ አይደለም።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም