ለሰው ልጅ ሁለንተናዊ ጤናማ አድገት መሰረት ለሆነው የጨቅላነት ጊዜ ተገቢው ትኩረት ሊሰጥ ይገባል ተባለ

106
አዲስ አበባ  ታህሳስ 8/2011 ለሰው ልጅ ጤናማ የአእምሮና የአካል እድገት መሰረት ለሆነው የጨቅላነት ጊዜ ተገቢው ትኩረት ሊሰጥ ይገባል ተባለ። በለጋ የልጅነት እድሜ ላይ የሚገኙ ህጻናት እድገት ላይ የሚያተኩር አውደ ጥናት ዛሬ በአዲስ አበባ ተጀምሯል። አውደ ጥናቱን የጤና ሚኒስቴር፣ የሴቶች፣ ወጣቶችና ህጻናት ጉዳይ ሚኒስቴር እና የትምህርት ሚኒስቴር በጋራ አዘጋጅተውታል። በዚሁ ጊዜ እንደተገለፀው ህጻናት ከጨቅላነት ጊዜያቸው አንስቶ የተሟላ ስብእና፣ መልካም ስነ-ምግባር፣ የዳበረ ስነ-ልቦናና ጤናማ የአእምሮ እድገት እንዲኖራቸው አድርጎ የመቅረጽ ጉዳይ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል። ይህም የህጻናት ሁለንተናዊ የአእምሮ፣ የስነ-ልቦና፣ የአመጋገብ፣ የጤና፣ የትምህርት እና ሌሎችንም ማህበራዊ እድገትን የሚያካትት መሆኑም ተመልክቷል። የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ድኤታዋ ዶክተር ሊያ ታደሰ እንደገለጹት፤ የበሽታ መከላከልን  ጨምሮ የተለያዩ ማህበራዊና ሌሎች አገልግሎቶችን ለህፃናት ማቅረብ ስኬታማ የሆነ ዜጋ ለማፍራት ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል። መንግስት ይህንን አገልግሎት በማረጋገጥ የህፃናትን ሞትና ህመም መከላከል ብሎም ብቁ ዜጋ ለማፍራት የሚያስችሉ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑንም ገልፀዋል። አውደ ጥናቱ ከአመጋገብ ጀምሮ እስከ አእምሮ መዳበር ድረስ ያለውን ባህል በማሻሻል ለህፃናት የጨቅላ እድሜ አድገት ትኩረት እንዲሰጥ ጠቀሜታ እንዳለውም ጠቁመዋል። የሴቶች፣ ወጣቶችና ህጻናት ጉዳይ ሚኒስትር ድኤታዋ ወይዘሮ አለሚቱ ኡሞድ በበኩላቸው፤ በመጀመሪያዎቹ 6 ዓመታት የእድሜ ክልል ከሌላው በላቀ ብሩህና ፈጣን የእድገት ደረጃ የሚስተዋልበትና ለቀጣይ ዘመንም ትልቅ መሰረት በመሆኑ የተለየ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አሳሰበዋል። እንደትምህርት እና ጤና ያሉ መሰረታዊ አገልግሎቶች ላይ መዋእለ ነዋይ ማፍሰስ ነገ በምላሹ ብቁና ተወዳዳሪ፣ ለአገሩ ተቆርቋሪና ጤናማ ትውልድን ለማፍራት አስፈላጊ መሆኑንም አመልክተዋል። በመሆኑም አገሪቱ በ2030 የቅድመ መደበኛ የትምህርት ተደራሽነትን በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች ላይ ለማዳረስና ብቁ ዜጋ ለማፍራት በእቅድ ይዛ እየሰራች ትገኛለች ሲሉ ገልፀዋል። ህጻናትን በአካልና በአእምሮ ለማዘጋጀት ለቅድመ ትምህርት ዝግጅት 20 በመቶ በመመደብ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የትምህርት ሚኒስቴር ተወካይ አቶ ያሳቡ ብርቅነህ ናቸው። የተባበሩት መንግሥታት የህፃናት መርጃ ድርጅት (UNICEF)፣ የአለም የጤና ድርጅት (WHO)፣ የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ኤጀንሲ (USAID፣ የአለም ባንክ እና ሌሎችም አጋር ድርጅቶች በተወካዮቻቸው አማካኝነት የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል። አውደ ጥናቱ ለሁለት ቀናት የሚቆይ ሲሆን በቀጣይም በከተማና በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ላይ የህጻናት እድገትና መዳበርን በሚመለከት በየአካባቢው ለሚገኙ ማህበረሰብ ክፍሎች፣ በጤና ተቋማት፣ በትምህርት ቤቶችና በሌሎችም ላይ የማሰተማርና ግንዛቤ የመፍጠር ተግባር ይከናወናል ተብሏል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም