ምክር ቤቱ ከዘጠኝ የዴሞክራሲ ተቋማት ጋር ተፈራረመ

86
አዲስ አበባ ታህሳስ 8/2011 የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በዜጎች መብቶች መከበር፣ በበጀት አጠቃቀምና በኦዲት ማስተካከያ ላይ ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ ከዘጠኝ የዴሞክራሲ ተቋማት ጋር የስራ ስምምነት ተፈራረመ። ስምምነቱን የፈረሙት የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትን ጨምሮ ዘጠኝ የዴሞክራሲ ተቋማት ናቸው። በምክር ቤቱ የህግ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ ፎዚያ አሚንና የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ መሐመድ የሱፍ ከተቋማቱ የስራ ኃላፊዎች ጋር ዛሬ ተፈራርመዋል። ተቋማቱ አስተዳደራዊ በደልን በማረምና በመከላከል፣ የመንግስት በጀትና ሐብት በአግባቡ ስራ ላይ መዋሉን ማረጋገጥ፣ የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲከበሩ ማድረግ፣ በስነ ምግባር የታነጸና ሙስናን የሚጸየፍ ትውልድ ማፍራት፣ የዜጎች የመምረጥና የመመረጥ መብት ማስከበር እንዲሁም የመድበለ ፓርቲ ስርዓት መገንባት ላይ ከፍተኛ ሚና አላቸው። ተጠሪነታቸው ለምክር ቤቱ የሆኑት ተቋማት የተጣለባቸውን ኃላፊነት በአግባቡ መወጣትና አለመወጣታቸውን ማዕከል ያደረገ የክትትል፣ የቁጥጥርና የድጋፍ ስርዓት መዘርጋቱን ምክር ቤቱ አስታውቋል። የዴሞክራሲ ተቋማቱ የሥራ ኃላፊዎች ''የተጣለብንን የህዝብና የመንግስት ኃላፊነት በአግባቡ እንወጣለን'' ሲሉ ፈርመዋል። ተቋማቱ የተሰጣቸውን ተልዕኮ በአግባቡ ከመወጣት አኳያ 70 በመቶ ፣የፋይናንስ አጠቃቀም 10 በመቶ፣ የኦዲት እርምጃ ማስተካከያ 10 በመቶ እንዲሁም ስርዓተ ጾታን ጨምሮ አካባቢ ጥበቃና ሌሎች ዘርፈ ብዙ ጉዳዮች የሚመዘኑባቸው መስፈርቶች ናቸው። የፌዴራል ዋና ኦዲተርና የፌዴራል ስነ ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን የስራ ኃላፊዎች ለኢዜአ እንዳሉት፤ እንዲህ ዓይነት አሰራር ምክር ቤቱንም ሆነ ተቋማቱን የሚመሩ የስራ ኃላፊዎች ስራቸውን በአግባቡ እንዲያከናውኑ የሚያስችል ነው። የፌዴራል ዋና ኦዲተር አቶ ገመቹ ዱቢሶ በሰጡት አስተያየት ''በዚህ መሰረት እንገመግማችኋለን ተብሎ ነው አሁን እኛም በዚህ መሰረት እንገመገማለን ብለን ነው ፊርማችንን ያኖርነው፤ በዚህ መሰረት አስቀድሜ እኔ ሃላፊነቴን መወጣት ካልቻልኩ ስራውን እለቃለሁ የምልበት ደረጃ ላይ እንድደርስ ያንን ካላልኩ ምክር ቤት የተሰጠህን ሃላፊነት በአግባቡ አልተወጣህም ስለዚህ  ይሄን ሃላፊነት ይዘህ መቀጠል አትችልም ብሎ  የሚያነሳበት ምናልባት በዚህ ሂደት ያበላሸው ነገር ካለ ጭምር የሚጠየቅበት ስርዓት ያበጀንበት ነው˝ ብለዋል። የፌዴራል ስነ ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር አቶ አየልኝ ሙሉዓለም በበኩላቸው''እኛም ግዴታችንን አውቀን በተፈራረምነው መሰረት ለመስራት እነሱም ደግሞ በፈረምነው መሰረት ለመጠየቅ የራሱ የሆነ አስተዋጽኦ እንዳለው ነው የማምነው፤ እነሱም ደግሞ እኛን ማገዝ የሚገባቸውን ተልዕኮችንን በአግባቡ መወጣት አንድንችል ለማድረግ ፤የእነሱን ሀላፊነት ለመወጣት እንዲችሉ ያደርጋቸዋል˝ ነው ያሉት። የህግ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ ፎዚያ አሚን እንዳሉት፤ ተቋማቱ ህዝብ የሚፈልገውን አገልግሎት ለመስጠት ግዴታ ገብተዋል። ተቋማቱ የሚመዘኑበትን መስፈርት የወጣ ሲሆን፤ ክትትልና ቁጥጥር ይደረግባቸዋል። ምክር ቤቱ ቀደም ሲል ሪፖርት በማድመጥና ግብረ መልስ በመስጠት በጅምላ የተቋማቱን ስራ የሚገመግምበት አሰራር መቅረቱን ተናግረዋል። ዘጠኙ የዴሞክራሲ ተቋማት የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ኤጀንሲ፣ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም፣ የፌዴራል የስነ ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን፣ የኢትዮጵያ ብሮድካስት ኮርፖሬሽን፣ የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን፣ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅትና የፌዴራል ዋና ኦዲተር ናቸው። ምክር ቤቱ ቀደም ሲል ከተለያዩ የመንግስት አስፈጻሚ መስሪያ ቤቶች ጋር ስምምነት ማድረጉ ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም