በደቡብ ኦሞ ለባለኃብቶች ከተሰጠው 160 ሺህ ሄክታር መሬት ውስጥ ስራ ላይ የዋለው 17 ሺህ ሄክታር ብቻ

103
አዲስ አበባ  ታህሳስ 8/2011 በደቡብ ብሔር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል ደቡብ ኦሞ ዞን በኢንቨስትመንት ዘርፍ ለተሰማሩ ባለኃብቶች ከሰጠው 160 ሺህ ሄክታር መሬት ውስጥ ስራ ላይ የዋለው 17 ሺህ ሄክታር ብቻ መሆኑን የዞኑ አስተዳደር አስታወቀ። ባለኃብቱ መሬቱን አጥረው ከማስቀመጥ ይልቅ ወደ ኢንቨስትመንት እንዲገቡ በተደጋጋሚ ውይይት መደረጉን የዞኑ አስተዳዳሪ አቶ አለማየሁ ባውዲ ገልጸዋል። ባለሃብቶቹ ወደ ስራ መግባት ያልቻሉት የመሰረተ ልማት፣ የብድርና መሰል ችግሮች ሳቢያ መሆኑን በተደረገ ምክክር ላይ የገለፁ ቢሆንም የተጠቀሱት ችግሮች አለመኖራቸውን ነው የዞኑ አስተዳደር የሚገልፀው። ''አንዳንዱ በመንግስት ተሰጥቶት አጥሮ ያሰቀመጠው መሬት የት እንደሚገኝ ጭምር ይረሳዋል'' ያሉት አቶ አለማየሁ ባለሐብቱ መሬት አጥሮ የመያዝ እንጂ ወደ ልማት የመግባት ቁርጠኝነት እንደሌለው ተናግረዋል። እንደ ዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ገለጻ በወቅቱ የመሬት አሰጣጥ ሂደቱ ችግር ነበረበት። በመሬት አሰጣጥ ላይ ያጋጠመውን ችግር ለመፍታት አዲስ አሰራር የተዘረጋ ሲሆን በአሁኑ ወቅት የሚሰጠው የመሬት መጠን ከ5 ሺህ እንዳይበልጥ  ተወስኗል ሲሉም አቶ አለማየሁ አስረድተዋል። ለልማት መሬት የወሰዱና ወደስራ ሳይገቡ አጥረው የቆዩ ባለሐብቶችን የማስመለስ ስራ መጀመሩን የተናገሩት ዋና አስተዳዳሪው በተያዘው ዓመት 25 ሺህ ሄክታር መሬት ወደ መሬት ባንክ መግባቱን ገልጸዋል። በዞኑ እስከ አሁን በከፊል ወደ ስራ የገቡ ባለኃብቶች እንዳሉ የጠቀሱት አስተዳዳሪው ባለኃበቶቹ በተያዘው ዓመት ውስጥ በሙሉ አቅማቸው ወደ ስራ መግባት እንደሚጠበቅባቸው ገልፀዋል። በተጠቀሰው ጊዜ ወደ ስራ የማይገቡ ከሆነ ግን የወሰዱትን መሬት ተመላሽ ያደርጋሉ ብለዋል። በግብርና፣ በማምረቻና ሌሎች ዘርፎች ለሚሳተፉ ባለሐብቶች ዞኑ 2 መቶ ሺህ ሄክታር መሬት ማዘጋጀቱን አስታወቋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም