ኢትዮጵያን ከኢኮኖሚያዊ ቀውስ ለመታደግ ሰላምና መረጋጋትን ማስፈን ይገባል

98
ታህሳስ 7/2011 በኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም በነበሩ አለመረጋጋቶች የደረሰው ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ድጋሜ እንዳይከሰት ህግ ሊከበር ይገባል ሲሉ ያነጋገርናቸው አመራሮችና ምሁራን ተናገሩ፡፡ ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ አንጻራዊ ሰላም ቢመጣም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አለመረጋጋቶች መፈጠራቸው እየተነቃቃ የነበረውን ኢኮኖሚ እንደሚያቀጭጨው የተናገሩት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ የሶስተኛ ዲግሪ ተማሪ አቶ መዚድ ናስር የመጣው ፖለቲካዊ ለውጥ በኢኮኖሚው ላይ አሉታዊ እና አዎንታዊ ጫና ይኖረዋል ይላሉ። በሽግግር ወቅት ኢንቨስተሮች መዋዕለ ንዋያቸውን ፈሰስ ለማድረግ መተማመኛ እስኪያገኙ ድረስ ኢንቨስትመንት ሊቀዘቀዝ እንደሚችልም ጠቁመዋል። የምጣኔ ሃብት ባለሙያው ፀጋ ዘዓብ ለምለም እንዳሉት የኢትዮጵያ ፖለቲካ ስልጣንን ማዕከል ያደረገ በመሆኑ ብዙ ጊዜ ለማህበረሰቡ የሚበጅ ኢኮኖሚያዊ ለውጥ ሲያመጣ አይታይም ነው ያሉት። እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ታዳጊ ሀገራት በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የሚፈጠር የበላይነትና ያለመግባባት ሽኩቻ በኢኮኖሚው ላይ የራሱ ተፅዕኖ ይኖረዋል ያሉት ፀጋዘዓብ ለምለም በርካታ ዜጎች መፈናቀላቸው፣ የኑሮ ውድነት መኖሩ፣ አለመረጋጋትና የሰላም መጥፋት ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ ስጋት መሆናቸውን ገልጿል። መንግስት በአሁኑ ወቅት ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን ብዙ በጀት እያወጣ መሆኑ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስን ስለሚፈጥር በሀገራዊ መግባባት ግጭቶችን በፍጥነት በማስቆም ለልማት ትኩረት መስጠት እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡ የኢትዮጵያ የንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ዋና ጸሃፊ አቶ እንዳልካቸው ስሜ በሀገሪቱ አሁን ካለው ለውጥ አኳያ ለኢኮኖሚው ተስፋና ፈተናዎች መኖራቸውን ገልጸዋል። የግሉ ዘርፍ በኢኮኖሚ ላይ የሚኖረው ሚና ከቃል ባለፈ እንዲተገበር መንግስት ስራዎችን ቢጀምርም፥ የግል ድርጅቶች በውጭ ምንዛሬና በግብዓት እጥረት እየተቸገሩ ነው ብለዋል። “አሁን በሀገሪቱ ያሉ አንዳንድ አለመረጋጋቶች የቢዝነስ ስራዎች ላይ ብዙ ጫና አልፈጠሩም፤ የባሰ ሁኔታ እንዳይፈጠርም ህግ ማስከበር ይገባል” ብለዋል። ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በርካታ አንድምታዎች ያለው ኢኮኖሚያዊ ጉዞ ተጀምሯል ያሉት   በገንዘብ ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ሀጂ ኢብሳ የሸቀጦች የዋጋ ግሽበት ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በየወሩ  ቅናሽ እያሳየ  መሆኑን ገልጸዋል። ባለፉት ጥቂት ዓመታት ኢትዮጵያ ውስጥ በነበረው አስጊ ሁኔታ የዋጋ ግሽበቱ ከአንድ አሃዝ ወደ ሁለት አሃዝ ከፍ እንዲልና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ እንዲፈጠር ማድረጉን ተናግረዋል። በአሁኑ ወቅትም በተወሰኑ አካባቢዎች የሚታዩ የፖለቲካዊ አለመረጋጋቶችና የውጭ ምንዛሬ እጥረት  የኢኮኖሚ ምርታማነት ላይ ችግሮችን መደቀናቸውን ነው አቶ ሀጂ ያነሱት። በሀገሪቱ ያሉ ኢኮኖሚያዊ ስጋቶችን ለመቅረፍ መንግስት የሀገሪቱን ሰላምና መረጋጋት በአስተማማኝ ሁኔታ ማስፈን ይገባዋል ያሉት አቶ መዚድ በየወሩ እየቀነሰ የሚገኘው የዋጋ ግሽበት እንዳይጨምር ስልት መንደፍ እና ህዝቡን ከኢኮኖሚያዊ ቀውስ የሚታደጉ ስልቶችን  መተግበር ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ አቶ ሀጂ በበኩላቸው ባለፈው ዓመት በአማካይ 17.7% ደርሶ የነበረው የዋጋ ግሽበት አሁን  በአማካይ ወደ 10.6% ወርዷል ነው ያሉት። ከሁለትና ሶስት ዓመታት በፊት የወደሙ ኢንቨስትመንቶችን ወደ ስራ ማስገባት እንደሚገባና አዳዲሶቹም መጥተው ኢንቨስት እንደያደርጉ መስራት ይገባል ነው ያሉት አቶ መዚድ  ። በዲፕሎማሲም ሆነ በሌላ መንገድ  የተለያዩ መንግስታት ድጋፍ ማድረጋቸውም የተዳከመውን የውጭ ምንዛሬ እጥረት እንደሚያስተነፍሰውና ሽግግር ላይ ያለው የሀገሪቱ ፖለቲካ ሲረጋጋ ኢኮኖሚውን የሚያነቃቁ የፖሊሲ እይታዎችን መፈተሽ እንደሚገባም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጠቁመው ነበር። በዚህ የሽግግር ወቅት ሊያጋጥሙ የሚችሉ ኢኮኖሚያዊ ስጋቶችን ለመፍታት መንግስት የፊስካል፣ የሞኒተሪና አስተዳደራዊ እርምጃዎችን እንደሚወስድም አቶ ሀጂ ገልጸዋል። “በአስተዳደራዊ እርምጃ የገንዘብ ቁጥጥርን ማጥበቅ ነው፣ ገበያውን በአቅርቦት ማረጋጋትና በተለይ ደሃው ህብረተሰብ ጫና እንዳይበዛበት ይሰራል” ነው ያሉት። አቶ መዚድ ናስር በበኩላቸው መንግስት በሙስኞችና ህገወጥ ነጋዴዎች ላይ እየወሰደ ያለው እርምጃ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው የላቀ በመሆኑ እርምጃውን እንዲያጠናክረው አስተያየታቸውን አክለዋል። እርምጃው የሀብት ክፍፍልን በማስተካከል ጥቂት ሰዎች ብቻ ሀብታም ከሆኑበት ስርዓት ብዙዎች የሀብት ፍትሐዊ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያስችላልም ነው ያሉት። ለአብነትም በአዲስ አበባ  በህገወጥ መንገድ ተይዘው የነበሩ ቤቶችን ለአቅመ ደካሞችና ለደሃ ደሃዎች ማከፋፈል መጀመሩ በፍትሃዊ የህብት ክፍፍል ላይ ድርሻው ላቅ ያለ ነው ብለዋል። መንግስት ሰላምና መረጋጋት ካሰፈነ በኋላ ኢኮኖሚ ነክ ፖሊሲዎችን በመቃኘት አዳዲስና ነባር አሰራሮችን በፍጥነት መተግበር እንዳለበትም  ነው የተናገሩት፡፡ የንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ዋና ጸሃፊው አቶ እንዳልካቸው የውጭ ኩባንያዎች አትዮጵያ አሁን ያለችበትን ሁኔታ እያጠኑ በመምጣት ላይ መሆናቸውን ገልፀዋል። የግል ዘርፉ ሀገራዊ ለውጡን ለማሳካት በተመቻቹ የንግድ አከባቢዎችን ገብቶ መስራት፣ የስራ እድል በመፍጠር ተጠቅሞ  እንዲጠቅሙ እየተሰራ ነው ብለዋል። በተለይ ጥራታቸውን የጠበቁ ምርቶች ለተጠቃሚው ማቅረብ ከጊዜያዊ ጥቅም ጋር የተገናኙ ህገወጥ ተግበራትን ማስወገድ አሁን በተጀመረው ለውጥ ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም