በኢትዮጵያ የማንበብ ባህል እንዳልዳበረ ተገለጸ

305
አዲስ አበባ  ታህሳስ 7/2011 በኢትዮጵያ  የማንበብ ባህል እንዳልዳበረና በቀን አንድ ገፅ ካለንባብ የሚያሳልፈው ዜጋ በርካታ መሆኑን የብሄራዊ ቤተመፃህፍትና ቤተመዛግብት ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡ በኢትዮጵያ የንባብ ባህልን ለማሳደግ በክልሎች ቤተመዛግብትና ቤተመፃህፍቶችን ለማደራጀት እየተሰራ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡ በህንድ አንድ ሰው በሳምንት 10 ሰዓት ከ 40 ደቂቃ የሚሆነውን ለንባብ የሚያውልባት አገር በመሆን በዓለም በአንደኝነት አንባቢ ዜጋ ያለባት አገር ሆና መመዝገቧን ወርልድ አትላስ ዶት ኮም የተሰኘው ገጸ-ድር አስፍሯል። የታይላንድ ዜጎች 9 ሰዓት ከ 24 ደቂቃ የቻይና ደግሞ 8 ሰዓት በሳምንት በማንበብ የዓለማችን ሁለተኛና ሦስተኛ ደረጃ አንባቢ ያላቸው አገሮች ናቸው። በማንበብ ባህል ከአፍሪካ ግብፅ ከዓለም አምስተኛ ስትሆን ደቡብ አፍሪካ 14ተኛ ደረጃ ላይ መቀመጧን ነው ወርልድ አትላስ ዶት ኮም ያሰፈረው። የብሄራዊ ቤተመፃህፍትና ቤተመዛግብት ኤጀንሲ የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ሽመልስ ታዬ ለኤዚአ እንደተናገሩት በኢትዮጵያ ግን  የማንበብ ባህል እንዳልዳበረና በቀን አንድ ገፅ ካለንባብ የሚያሳልፈው ዜጋ በርካታ ነው  ። በአገሪቱ ካለው የሕዝብ ቁጥር አንፃር የአንባቢው ቁጥር ዝቅተኛ ቢሆንም መሻሻል እያሳየ መሆኑንም ዳይሬክተሩ አስገንዝበዋል። የኅብረተሰቡን የንባብ ባህል ለማሳደግም ኤጀንሲው ከ2006 ዓ.ም ጀምሮ በሁሉም ክልሎች ለሳምንት የሚዘልቅ የንባብ ሳምንት ከማዘጋጀት ባሻገር የመፅሀፍት አውደ ርዕይ ሲያዘጋጅ መቆየቱን አስረድተዋል። ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመተባበር የንባብ ምሽት በማዘጋጀት የንባብ ባህልን ለማሳደግ የተሰራ መሆኑን የተናገሩት ዳይሬክተሩ መሻሻሎች እየታዩ መምጣታቸውን በአካባቢዎቹ ባለው የመፅሀፍት ፍላጎት ሽያጭ ለማወቅ እንደተቻለ ገልጸዋል። "የንባብ ባህላችን ቢታይ ምናልባት አንድ ሰው በቀን አንድ ገፅ እንኳን ሳያነብ የሚውልበት ሁኔታ እንዳለ ያሳያል" ያሉት አቶ ሽመልስ በቀጣይ የአንባቢውን ቁጥር ለማሳደግ በየክልሉ የቤተመዛግብትና ቤተመፃህፍትን ከማደራጀት በተጨማሪ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ነው  ብለዋል። እንደ ዳሬክተሩ ገለጻ ባልተጣራ መረጃ ብዙ ህዝብ የሚዋከብበት ሰላም የሚደፈርስበት ሁኔታ ያለ በመሆኑ ህብረተሰቡ በማንበብ በመረጃ የበለጸገ በመሆን ከእንደዚህ  አይነት ችግር አገርን መጠበቅ  ይገበዋል ፡፡ በጉለሌ ክፍለ ከተማ የወረዳ 5 ወጣት ማዕከል የቤተ መጽሐፍት ባለሙያ ወይዘሮ እታገኝ ሙላት በተለይ ቤተ መፅሐፍቱ ለእድሳት ተብሎ ከአንድ አመት በላይ ተዘግቶ በመቆየቱ የተጠቃሚው ቁጥር መቀነሱን ነግረውናል። የተጠቃሚውን ቁጥር ከፍ ለማድረግ በራሪ ወረቀቶችና ሌሎች መንገዶችን በመጠቀም እየተሰራ መሆኑንም ገልፀውልናል።  አስተያተቻውን ለኢዜአ የሰጡ መፃህፍት ሻጮችና ገዢዎችም መፅሀፍትን የሚገዛው ቁጥር አናሳ መሆኑንና ከገዢውም ውስጥ አብዛኛውን የሚይዙት በእድሜ የገፉ ሰዎች መሆናቸውን ይናገራሉ። በተለይ ወጣቱ መፅሀፍት በማንበብ እውቀት መሸመት እንዳለበትና ጊዜውን ለንባብ ማዋል እንደሚጠበቅበት ተናግረዋል። አለሙ ተካ የተባሉ መፅሀፍ ሻጭ  እንደተናገሩት መጽሀፍ አንባቢው በጣም ጥቂት መሆኑን ጠቅሰው በተለይ ወጣቱ መጽሀፍ ገዝቶ የማንበብ ባህሉ አናሳ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡ መጽሀፍ ገዝቶ ማንበብ እውቀትን ከማስፋት በተጨማሪ ከአልባሌ ቦታ ከመዋል ይጠበቃል የሚሉት አቶ ታደሰ ወልደፃዲቅ የተባሉ መፅሀፍ ገዢ መጽሀፍን በማንበብ በእውቀት ጎዳና በመራመድ አገሩን ወደፊት መራመድ ይገባል ብለዋል፡፤ ኅብረተሰቡ የተለያዩ መፅሀፍትን በማንበብ የንባብ ባህሉን ማሳደግና ለሀገር ጠቃሚ ትውልድ መፍጠር እንደሚገባም አስተያየት ሰጪዎቹ ተናግረዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም