የሚኒስትሮች ምክር ቤት በሶስት ረቂቅ ደንቦችና በስድስት የስምምነት ረቂቅ አዋጆች ላይ ውሳኔ አሳለፈ - ኢዜአ አማርኛ
የሚኒስትሮች ምክር ቤት በሶስት ረቂቅ ደንቦችና በስድስት የስምምነት ረቂቅ አዋጆች ላይ ውሳኔ አሳለፈ

አዲስ አበባ ታህሳስ 6/2011 የሚኒስትሮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 58ኛ መደበኛ ስብሰባ በሶስት ረቂቅ ደንቦችና በስድስት የስምምነት ረቂቅ አዋጆች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ ማሳለፉን አስታወቀ። ምክር ቤቱ በቅድሚያ የተወያየው የመንግስት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ኤጀንሲን ተግባርና ሃላፊነት ለመወሰን በተዘጋጀ ረቂቅ ደንብ ላይ ነው፡፡ ኤጀንሲው በፌዴራል መንግስት አስፈጻሚ አካላት አደረጃጀት ላይ የተደረገውን ለውጥ ተከትሎ የመንግስት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ኤጀንሲ የፌዴራል መንግስት አስፈጸሚ አካላት ስልጣንና ተግባር ለመወሰን በወጣው አዋጅ ቁጥር 1097/2011 አንቀጽ 32/15 መሰረት የተቋቋመ ነው። በመሆኑም ኤጀንሲው የልማት ድርጅቶችን ስትራቴጂካዊ በሆነ መንገድ በመምራት በሀገር አቀፍና አለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ሆነው የመንግስትን የልማት ፖሊሲ መደገፍ እንዲችሉ ለማድረግ የገንዘብ ሚኒስቴር የኤጀንሲውን ስልጣንና ተግባር ለመወሰን ረቂቅ ደንብ አዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምክርቤት ውሳኔ አቅርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በቀረበው ረቂቅ ደንብ ላይ በስፋት ከተወያየ በኋላ አንዳንድ ማስተካከያዎችን በማከል ደንቡ በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ እንዲወጣና በስራ ላይ እንዲውል ወስኗል፡፡ ምክር ቤቱ ቀጥሎ የተወያያው የስፖርት ኮሚሽንን ስልጣን፣ ተግባርና አደረጃጀት ለመወሰን እና የብሔራዊ ስፖርት ምክር ቤትን ለማቋቋም የተዘጋጀ ረቂቅ ደንብ ላይ ነው፡፡ የፌዴራል መንግስት አስፈጸሚ አካላት ስልጣንና ተግባር ለመወሰን የወጣው አዋጅ ቁጥር 1097/2011 አንቀጽ 32/4 መሰረት የስፖርት ኮሚሽን የተቋቋመ በመሆኑ የኮሚሽኑን ስልጣንና ተግባር የሚወስን ደንብ ማውጣት አስፈላጊ መሆኑን ምክር ቤቱ ጠቅሷል። በአገር አቀፍ ደረጃ ስፖርትን ለማስፋፋትና ህዝባዊ ለማድረግ ስፖርቱን በበላይነት የሚመራና የሚያስተባብር ብሔራዊ የስፖርት ምክር ቤት ማቋቋም አስፈላጊነቱ ስለታመነበት የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ረቂቅ ደንብ ተዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምክርቤት አቅርቧል፡፡ ሌላው ምክር ቤቱ የተወያየው በኢነርጂ ረቂቅ ደንብ ላይ ነው። በ2006 ዓ.ም ከወጡ ሕጎች የኢነርጂ ዘርፍ የሕግ፣ የቁጥጥር እና ተቋማዊ አደረጃጀት ማዕቀፎች ውስጥ የኢነርጂ አዋጅ ቁጥር 810/2006 እና የኢትዮጵያ ኢነርጂ ባለስልጣን ማቋቋሚያ ደንብ ቁጥር 308/2006 በዋናነት ይጠቀሳሉ፡፡ ይህ ረቂቅ ደንብም የተዘጋጀው በነዚህ ሁለት ሕጎች አማካይነት የተፈጠሩትን አስቸኳይ ሁኔታዎች በአግባቡ በስራ ላይ እንዲውሉ ለማድረግ ሲሆን፤ የውሃ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር የኢነርጂ ረቂቅ ደንብ አዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምክርቤት ውሳኔ አቅርቧል፡፡ ምክርቤቱም በቀረበው ረቂቅ ደንብ ላይ በስፋት ከተወያየ በኋላ አንዳንድ ማስተካከያዎችን በማከል ደንቡ በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ እንዲወጣና በስራ ላይ እንዲውል ወስኗል፡፡ በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ እና በአልጄሪያ ህዝባዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግሥት መካከል የተደረገውን የንግድ፣ የመገናኛ ብዙኃን፣ የእንስሳት እና አሳ እርባታ እንዲሁም የዕጽዋት ማቆያ እና ጥበቃ የተደረጉትን ስምምነቶች ለማጽደቅ የቀረቡ ረቂቅ አዋጆች ሌሎቹ ምክር ቤቱ የተወያየባቸው ጉዳዮች ናቸው። ምክር ቤቱ ለአገራቱ የሚያስገኘውን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ከግምት ውስጥ በማስገባት ረቂቅ አዋጆቹን ተቀብሎ ይጸድቁ ዘንድ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፉ ወስኗል፡፡ በመጨረሻ ምክር ቤቱ የተወያየው በኢትዮጵያ እና በኳታር መንግሥት መካከል የዲፕሎማቲክ እና የሰርቪስ/ልዩ ፓስፖርት ለያዙ ሰዎች ቪዛን ለማስቀረት የተደረገውን የትብብር ስምምነት ለማጽደቅ የቀረበ ረቂቅ አዋጅ እና የአጠቃላይ ትምህርት፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እና ሳይንሳዊና ምርምር ዘርፍ ትብብር የመግባቢያ ሰነድን ለማጽደቅ በቀረበ ረቂቅ አዋጅ ላይ ነው። በአዋጁ ላይ ከተወያየ በኋላም ስምምነቱ የሁለቱን አገራት ወዳጅነት ከማጠናከሩም በላይ ያለውን ትስስር ወደ ተሻለ ደረጃ እንደሚያደርስ ስለታመነበት ረቂቅ አዋጆቹ ተቀብሎ ይጸድቁ ዘንድ ለህዝብ ተወካዮች ምክርቤት እንዲተላለፉ ወስኗል፡፡