የቀድሞው ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ የቀብር ስነ-ስርአት በመጪው ረቡዕ ይከናወናል

106
አዲስ አበባ ታህሳስ 6/2011 የቀድሞው ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ ቀብር በመጪው ሳምንት እለተ ረቡዕ በታላቅ ስነ-ስርዓት እንደሚከናወን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ። ሚኒስትር ዴኤታዋ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ የቀድሞውን ፕሬዚዳንት ህልፈተ ህይወትና የቀብር ስርዓት ዝግጅትን በተመለከተ ዛሬ ማምሻውን መግለጫ ሰጥተዋል። አምባሳደሯ እንዳሉት ስርዓተ ቀብሩን በታላቅ ክብር ለማከናወን የሚያስችል ኮሚቴ ተቋቁሟል። የጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣  የመከላከያ ሚኒስቴር፣ የገንዘብ ሚኒስቴር እና ሌሎች የመንግስትና የሃይማኖት ተቋማትን ያካተተ ንኡሳን ኮሚቴዎችን የያዘው አብይ ከሚቴ በዛሬው እለት ተግባራዊ ሥራ ጀምሯል። የቀብር ስነ-ስርአቱ ቤተሰቦቻቸው፣ የመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት፣ ወዳጅ ዘመዶቻቸው በተገኙበት የፊታችን ረቡዕ ከቀኑ 9 ሰአት በቅድስት ስላሴ ካቴድራል ቤተ ክርስቲያን እንደሚከናወንም ተናግረዋል። በአዋጅ ቁጥር 653/2005 አንቀፅ 11 መሰረት ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ከዚህ አለም በሞት ሲለዩ ብሄራዊ ሃዘን እንደሚታወጅና ለአንድ ቀን የሃገሪቱ ባንዲራ ዝቅ ብሎ እንደሚውለበለብ ይደነግጋል። ለቀድሞው ፕሬዚዳንትም ይኸው ስርዓት ይፈፀማል ተብሎ ይጠበቃል። የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በመጪው ሳምንት ማክሰኞ ተሰብስቦ የብሄራዊ ሃዘኑን ቀን እንደሚወስን ይጠበቃል። የቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት አቶ ግርማ ወልደጊዮርጊስ በተወለዱ በ95 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት ትናንት ሌሊት ነው። አቶ ግርማ ከአንድ ዓመት በፊት በሞት ከተለዩአቸው ባለቤታቸው አምስት ልጆችን አፍርተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ አህመድ ዛሬ ባስተላለፉት የሀዘን መልዕክት የቀድሞው ፕሬዚዳንት አቶ ገርማ በዕውቀታቸውና በሙያቸው ለሕዝባቸው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የሰጡ፣ የታታሪነት፣ የቅንነትና፣ የሕዝባዊ አገልግሎት ሰጭነት ተምሳሌት እንደነበሩ ገልፀዋል። ፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴም በበኩላቸው " የቀድሞው ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ ኢትዮጵያችንን ከወጣትነት ዘመናቸው ጀምሮ በከፍተኛ የሃገር ፍቅር ስሜት ያገለገሉ እና በአስቸጋሪ ውጣ ውረዶች ውስጥ በመገኘት ለሃገራቸው ያላቸውን ክብር በተግባር ያሳዩ ታላቅ ባለውለታ ናቸው" ብለዋል። አቶ ግርማ ከ1994 እስከ 2006 ዓም የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት በመሆን አገልገለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም