የባህል ኢንዱስትሪው ዘርፍ ለሀገሪቱ እድገት ጉልህ ሚና እንዲኖረው የሚያግዝ ጥናት ተካሄደ

789

አዳማ ታህሳስ 6/2011 የባህል ኢንዱስትሪው ዘርፍ  በሀገሪቱ ልማትና እድገት ውስጥ ጉልህ ሚና እንዲኖረው የሚያግዝ ጥናት መካሄዱን የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

በዘርፉ የተካሄደውን ጥናት ለባለድርሻ አካላት ለማስተዋወቅና ግብዓት ለማሰባሰብ ያለመ የምክክር መድረክ ዛሬ በአዳማ ከተማ ተጀምረዋል።

በዚህ ወቅት በሚኒስቴሩ የባህል ዘርፍ አማካሪ አቶ ገብርኤል አስፈው እንደገለጹት ጥናቱ የተካሄደው የሀገሪቱን እምቅ የብዝሃ ባህል ሀብት በኢኮኖሚያዊ ልማትና እድገት ውስጥ ጉልህ ሚና እንዲኖረው በኢንቨስትመንት  አማራጮች ኮድ እንዲመዘገብ ለማስቻል ነው።

ጥበባዊና ፈጠራዊ የባህል ምርቶች ለዜጎች ሀብት ማፍራትና ለወሳኝ የገቢ ምንጭ ሆኖ እንዲያገለግል ብሎም  ዘመናዊ የባህል ኢንዱስትሪ ልማት ለማስፋፋት ያለመ ጥናት መሆኑን አመልክተዋል።

የባህል ኢንዱሰትሪ ልማት ዋና ዓላማው ቅርሶችን፣ ጥበባዊና ፈጠራዊ የባህል ምርቶችን በአግባቡ ለማልማት፣ በሀገር ውስጥና በውጭ  ማስተዋወቅና በገበያው ዘልቆ መግባት የሚችል የኢንቨስትመንተ አማራጭ ለመዘርጋት ጭምር እንደሆነ ተናግረዋል።

ባህል ለሀገር ልማትና እድገት ቀጣይነት ድርሻው የጎላ መሆኑን የገለጹት ደግሞ በመድረኩ ላይ ጥናቱን ያቀረቡት በሚኒስቴሩ የባህል ተቋማት ልማት ባለሙያ አቶ ተፈሪ ተክሉ ናቸው።

ጥናቱ የባህል ምርቶች፣ አገልግሎቶችና ቅርሶች  በዘመናዊ መልክ ለማልማት ፣ ለማስተዋወቅና ሰፊ የሥራ እድል የሚፈጠርበት መስክ ማድረግ የሚያስችል የህግ ማእቀፎች፣ ፖሊስዎችና ስትራቴጂዎች በአዲስ መልክ እንዲቀየሱ ለማድረግ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ባለሙያው “በዋናነት በዘርፉ ትኩረት ያለመስጠትና ግልፅ የሆነ ዓልም አቀፍ ይዘቱን የጠበቀ የባህል ማዕከላት ግንባታና ማደራጀት፣ የቦታ፣ የብድር አገልግሎት፣ የሰው ሃይሉን ማብቃት የሚችሉ ደረጃቸውን የጠበቁ ትምህርትና ስልጠና ያለመኖር በጥናቱ የተመለከቱ ችግሮች ናቸው”ብለዋል።

በሀገር ውስጥ የሚዘጋጁ ፊልሞች፣ የኪነ ጥበብና የፈጠራ ሥራዎች በተገቢው መንገድ ለማስተዋወቅ ድጋፍ ማድረግ፣ በዘርፉ ለሚሰማሩ ባለሃብቶችና ድርጅቶች ሁሉን አቀፍ የኢንቬስትመንት እገዛ ለማድረግ እንደሆነ አመልክተዋል።

ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል አርቲስት ደሳለኝ ኃይሉ እንዳለው የባህል ኢንዱስትሪውን ዘርፍ በዘመናዊ መልኩ ማልማት በዋናነት በሀገሪቷ የሥራ አጥነትን በመፍታት ለድህነት ቅነሳ  ጉልህ ሚና ይኖረዋል።

የብሔር ብሔረሰቦች  ባህል በእኩልነት ማልማት አሁን በሀገሪቱ የሚስተዋሉ ችግሮችን በማስወገድ አንድነት እንዲጎለብት እንደሚያስችል ተናግሯል፡፡

ከዚህ  ባሻገርም  ወሳኝ የቱሪዝምና የውጭ ምንዛሪ ምንጭ በማድረግ ልማትና እድገትን በአስተማማኝ ሁኔታ ለማስቀጠል ቁልፍ ሚና ያለው መሆኑን ገልጸዋል።

“በዘርፉ የሚከናወኑ የኢንቨስትመንት ሥራዎችን መለየት፣ የህዝቦችን ባህል እርስ በራስ እንዲመጋገብ፣ ያላቸውን ትስስር ማጤንና አንዱ ለሌላው ግብዓት በሚሆንበት መልኩ የዘርፉ ኢንዱስትሪ ልማት ሊከናወን ይገባል” ብለዋል።

ጥናቱ የተካሄደው በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር  ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከአርቲስቶች ጋር ውይይት ባደረጉበት ወቅት በሰጡት አቅጣጫ መሰረት ባለፉት ሰባት ወራት ውስጥ የተከናወነ መሆኑ ተመልክቷል፡፡

ለሁለት ቀናት በሚቆየው መድረክ ላይ ከኢንቨስትመንት ኮሚሽን፣ ከቱሪዝም ድርጅቶች፣ አርቲስቶችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ነው፡፡