ሰብአዊ መብት ጥሰት የፈጸሙ አካላት ለህግ እንዲቀርቡ የሚደግፉ መሆናቸውን በመቱ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ

98
መቱ ታህሳስ 6/2011 በዜጎች ላይ የከፋ ሰብአዊ መብት ጥሰት የፈጸሙ አካላትን ለህግ ለማቅረብ መንግስት እያሳየ ያለውን ቁርጠኝነት እንደሚደግፉ የመቱ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡ ነዋሪዎቹ ለኢዜአ እንዳሉት ባለፉት ዓመታት ህገመንግስቱን በመጣስ በአንዳንድ የደህንነትና ጸጥታ አካላት የተፈጸመው የመብት ጥሰት በዜጎች ላይ ከፍተኛ የሞራልና የአካል ጉዳት አድርሷል፡፡ ከነዋሪዎቹ መካከል ቀሲስ ወልዱ መቼሶ በሰጡት አስተስተያየት በሀገሪቱ በስውር እስር ቤቶች ጭምር ሲፈጸሙ የነበሩ የመብት ጥሰቶች የሚያሳዝን አስነዋሪ ተግባር መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ አመርቂ ለውጥ ያመጣ ያለው አመራር ችግሮችን ከስሩ ለመፍታት እያደረገ ያለው ጥረት የሚበረታታ መሆኑን ገልጸው ከለውጥ ኃይሉ ጎን በመሆን የሚጠበቅባቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል፡፡ አቶ ደምሴ ደበላ የተባሉ ነዋሪ በበኩላቸው በዜጎች ላይ የተፈጸመው የመብት ጥሰትና የደረሰው ጉዳት ዳግም እንዳይከሰት መንግስት በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡ "በሀገሪቱ ዲሞክራሲያዊ ስርአት ተገንብቶ ዜጎች በህግና በህሊና የሚዳኙበት አሰራር ሊዘረጋና ስልጣን የህዝብ አደራ መሆኑ የሚረጋገጥበት አመራር ሊኖር ይገባል" ብለዋል፡፡ በሀገሪቱ ባለፉት ዓመታት የዲሞክራሲያዊና ሰብአዊ መብቶች ከመከበር ይልቅ እየተቀበሩና እየተሸረሸሩ መምጣታቸውን የገለጹት ደግሞ ሌላው የከተማው ነዋሪ አቶ በቀለ ጎዱ ናቸው፡፡ መንግስት ህገመንግስቱን ለማስከበርና የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ እያሳየው ያለውን ቁርጠኝነት አጠናክሮ እንዲቀጥል የሚደግፉ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ወይዘሮ አርፋሴ ገምቴሳ የተባሉት ነዋሪ በበኩላቸው "ለረዥም ዓመታት ጥፋት ሲፈጽሙ የነበሩ ግለሰቦችን  መንግስት ተከታትሎ ለህግ ሊያቀርብ ይገባል" ብለዋል፡፡ ከአሁን በኋላ ተመሳሳይ ጥፋት በሀገሪቱ ሊፈጸም እንደማይገባ ጠቁመው የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድን ምሳሌን በመከተል ከሁሉም ጋር በፍቅር፣  በአንድነትና በእኩልነት ተሰስቦ ለውጡ እንዲቀጥል የበኩላቸውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል፡፡ "ህገመንግስቱን በመጣስ በማንአለብኝነት የከፋ ሰብአዊ መብት ጥሰት የፈጸሙ ግለሰቦች አንድ በአንድ ተይዘው ለፍርድ መቅረብ አለባቸው "ያሉት ደግሞ  አቶ ነስሩ አህመድ ናቸው፡፡ መንግስት እንደመንግስት የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ እያሳየ ያለውን ቁርጠኝነት አጠናክሮ እንዲቀጥል የሚደግፉ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም