የታራሚዎችን ሰብአዊ መብት በመጠበቅ አምራች ዜጋ ለማፍራት እንሰራለን- ተመራቂ የማረሚያ ፖሊስ አባላት

1154

አዲስ አበባ ታህሳስ 6/2011 የታራሚዎችን ሰብአዊ መብት በመጠበቅ አምራች ዜጋ ለማፍራት እንደሚሰሩ በመካከለኛ አመራርና በአድማ ብተና ሰልጣኝ የማረሚያ ቤት ፖሊሶች ተናገሩ።

አለልቱ የሚገኘው የፌዴራል ማረሚያ ቤት በመካከለኛ አመራርና በአድማ ብተና ወታደራዊ ሙያ የሰለጠኑ 428 የማረሚያ ቤት ዕጩ መኮንኖችና የአድማ ብተና ፖሊሶች የፌዴራልና የክልል ማረሚያ ቤት ኃላፊዎች በተገኙበት በተካሄደው ስነ-ስርዓት ዛሬ ተመርቀዋል።

ለኢዜአ አስተያይታቸውን የሰጡ ሰልጣኝ መኮንኖች ስልጣናው ከዚህ በፊት በማረሚያ ቤት አካባቢ የነበረውን ችግሮች በመቅረፍ፣ የታራሚዎችን ሰብዓዊ መብት ጠብቆ አገልገሎት መስጠት እንደሚቻል ግንዛቤ ያገኙበት መሆኑን አንስተዋል።

ረዳት ሰርጀንት አብደታ ደሬሳ ከቃሊቲ ማረሚያ ቤት እንደተናገሩትእርምጃ ከመውሰድ በፊት  ምክክር በማድረግ ታራሚዎችን አብቅተን፤ ሰባዊና ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን ጠብቀን ለማውጣት እንሰራለን ብለዋል፡፡

ከአዲስ ለውጥ ጋር አብሮ ለመሄድ አዲስ ሰው ሆነን ሰዎች በሃይል ከመያዝ በአዕምሮ ላይ በመስራት የአስተሳሰብ ለውጥ ለማምጣት እንደሚያገለግሉ የተናገሩት ድግሞ  ረዳት ኢንስፔክተር ከማል ሰይድ ኦሮሚያ ማረሚያ ቤት ፖሊስ ናቸው፡፡

ከምንም በላይ ለሰው ልጅ ክብር  በመስጠት በተገቢው መልኩ በመያዝ መልካምና አምራች ዜጋ በማፍራት ወደ ህብረተሰቡ ለማቀላቀል መንግስትና ህዝብ የሰጠንን አደራ ለመወጣት ዝግጁ ነን ብለዋል ረዳት ኢንስፔክተሩ፡፡

ስልጠና ሲሰጡ ከነበሩት መካከል ረዳት ሰርጀንት አባይ ከበደና ዋና ሳጀን አብርሃም ገብረ ክስርቶስ እንደተናገሩት፣ በስልጠናው የፖሊስ አባላቱ በእስረኞች አያያዝና አጠባበቅ የተሻለ ግንዛቤ እንዲኖራቸው የሚያስችል ጥሩ ትምህርት መስጠታቸውንን ገልጸዋል።

ረዳት ሰርጀንት አባይ ከበደ በበኩላቸው ስልጠናው ከታራሚ ጋር ያለው ግንኙነት እንደሆነ ገልጸው ፋይዳው ሌላ ነገር ሳይጠቀሙ ታራሚን በመምከርና እርስ በራሳቸውም ተመካክረው ለውጥ እንዲያመጡ የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡

የፌዴራል ማረሚያ ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ጀማል አባስ የማረሚያ ቤት ዋና ዓላማ በተለያዩ ወንጀሎች በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ወደ ተቋሙ የሚመጡ የቀጠሮ እስረኞችና የሕግ ታራሚዎቸን በመቀበል ከወንጀለኝነት ባህሪ ተላቀው አምራችና ሕግ አክባሪ ዜጋ እንዲሆኑ ማስቻል ነው።

ይህን ዓላማ ማሳካት የሚቻለው ግን የማረሚያ ቤት ጥበቃ አባላት በወታደራዊና ዲሲፕሊን በጥራት ሰልጥነው የአገልጋይነት መንፈስ ሲላበሱ ነው ብለዋል።

የማረሚያ ቤቱ ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ስርዓተ ትምህርት ከወቅቱ ተለዋዋጭ ሁኔታ ጋር ተጣጥሞ እንዲሄድ የስርዓተ ትምህርት ክለሳ ስራ እየተከናወነ መሆኑንም ተናግረዋል።

ከቅርብ ጊዜ ወደህ አገራዊ ለውጡን ተከትሎ ማረሚያ ቤቶች በሰብአዊ መብት፣ በማህበራዊ አገልግሎትና አስተዳደርና ፍትህ ጉዳዮች ላይ የነበሩ ችግሮች እየተሻሻሉ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የመካከለኛ አመራር ስልጣናው ዓላማም እነዚህ ለውጦች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ማድረግ እንደሆነ ነው ያብራሩት።

በመሆኑም ተመራቂዎች ወደስራ ቦታቸው ሲመለሱ በሰብዓዊ መብት አያያዝ፣ በማረምና ማነጽ ተግባራት፣ ሕገ መንግስቱን በመጠበቅ ታራሚዎችን በቅንነትና ታማኝነት እንዲያገለግሉ ጥሪ አቅርበዋል።

ሰልጣኞቹ የመስክ ወታደራዊ ስልጠናዎችን የንድፈ ሃሳብ ትምህርቶችን የወሰዱ ሲሆን 149ዎቹ ለአንድ ወር ከአስራ አምስት ቀን ለአድማ ብተና፤ ቀሪዎቹ 279 ያህሉ ደግሞ በመካከለኛ አመራር ዕጩ መኮነንነት ለሶስት ወራት የሰለጠኑ ናቸው።

ከሰልጣኞቹ መካከል 43ቱ ሴቶች ናቸው።

ስልጠናውም ከወታደራዊ እንቅስቃሴዎች ባሻገር ህገ መንግስትና ሰባዊ መብት፣ የወንጀል ህግ፣ አድማ፣ አደጋና ወንጀል መከላከል፣ አዋጆችና ደንቦች፣ የፖሊስ ስነ ምግባር፣ ስራ አመራር፣ ተሃድሶ ልማት፣ የለውጥ ስራ አመራር ትምህርቶችን ያካተተ መሆኑ ተጠቅሷል።