ፕሬዚዳንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ በቀድሞው ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ ሞት ማዘናቸውን ገለፁ

112
አዲስ አበባ ታህሳስ 6/2011 ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ በቀድሞው ፕሬዚደንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ ሞት የተሰማቸውን ሀዘነ ገለፁ። ፕሬዚዳንቷ በዚሁ የሀዘን መግለጫቸው "የቀድሞው ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ ኢትዮጵያችንን ከወጣትነት ዘመናቸው ጀምሮ በከፍተኛ የሃገር ፍቅር ስሜት ያገለገሉ እና በአስቸጋሪ ውጣ ውረዶች ውስጥ በመገኘት ለሃገራቸው ያላቸውን ክብር በተግባር ያሳዩ ታላቅ ባለውለታ ናቸው" ብለዋል፡፡ አክለውም ለ12 ዓመታት በፕሬዚዳንትነት ካገለገሉበት ከፍተኛ ሃገራዊ ሃላፊነት በተጨማሪ እየተመናመነ የመጣውን የደን ሽፋን መልሶ እንዲያገግም ግንባር ቀደም የአረንጓዴ ልማት አርበኛ በመሆን ከፍተኛ አስተዋጽዎ ማድረጋቸውንም አውስተዋል። አቶ ግርማ "ጧሪና ደጋፊ ያጡ ወገኖቻችን ትኩረት እንዲያገኙ ሲያደርጉት የነበረው ጥረትም ሁሌም በመልካም ተግባራቸው እንድናስታውሳቸው የሚያደርገን ነው" ሲሉም ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ገልፀዋል፡፡ በመጨረሻም ፕሬዚዳንቷ በአቶ ግርማ ህልፈት የተሰማቸውን ጥልቅ ሃዘን በኢትዮጵያ ህዝብና በራሳቸው ስም ገልፀዋል። ለወዳጅ ዘመዶቻቸውም መጽናናትን ተመኝተዋል። አቶ ግርማ ወልደጊዮርጊስ በተወለዱ በ95 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት ትናንት ሌሊት ነው። አቶ ግርማ ከአንድ ዓመት በፊት በሞት ከተለዩአቸው ባለቤታቸው አምስት ልጆችን አፍርተዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም