ኢንተርናሽናል ዳኛ በአምላክ ተሰማ የዓለም የክለቦች ሻምፒዮና የሩብ ፍፃሜ ጨዋታ ይመራሉ

86
አዲስ አበባ ታህሳስ 6/2011 ኢትዮጵያዊው ኢንተርናሽናል ዳኛ በአምላክ ተሰማ የዓለም የክለቦች ሻምፒዮና የሩብ ፍፃሜ ጨዋታ እንዲመሩ በፊፋ ተመረጡ። በተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች በመካሄድ ላይ ያለው የፊፋ የዓለም ክለቦች ውድድር ባለፈው ረቡዕ የተጀመረ ሲሆን ዛሬ በሁለት የሩብ ፍፃሜ ጨዋታዎች የሚቀጥል ይሆናል። ዛሬ ከቀኑ በ10:00 ሠዓት 22 ሺህ117 ተመልካቾችን በሚይዘው ሃዛ ቢን አልዛይድ ስታዲየም የሜክሲኮው ክለብ ቺቫስ እና የጃፓኑ ካሽማ አንትለርስ የሚያደርጉትን ጨዋታ ኢንተርናሽናል ዳኛ በአምላክ ተሰማ እንዲመሩ ተመርጠዋል። የሱዳኑ ዋሌድ አህመድ እና የደቡብ አፍሪካው ዛክሌ ዚሆላ ጨዋታውን በረዳት ዳኝነት ይመሩታል። ኢንተርናሽናል ዳኛ በዓምላክ ተሰማ የካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ ሁለት የፍፃሜ ጨዋታዎችን፣ የአፍሪካ ዋንጫ፣ የቻን ውድድርና የማጣሪያ ጨዋታዎችን መርተዋል። በ2018 የዓለም ዋንጫ ጨዋታዎችም በአራተኛ ዳኝነት መመደባቸው ይታወሳል። በተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች አስተናጋጅነት በሚካሄደው የዓለም የክለቦች ሻምፒዮና ውድድር የስድስት አህጉራት የክለብ ውድድሮች አሸናፊዎች እየተሳተፉ ነው። የአርጀንቲናው ሪቨር ፕሌት፣ የኒውዚላንዱ ቲም ዌሊንግተን፣ የስፔኑ ሪያል ማድሪድ፣ የሜክሲኮው ጓድላሀራ፣ የቱኒዝያው ኤስፔራንስ ቱኒስ፣ የጃፓኑ ካሺማ ሐንትለርስ እና የተባበሩት ዓረብ ኢምሬቶቹ አል አይን ክለቦች ተሳታፊዎች ናቸው።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም