በዜጎች ላይ እየደረሱ ያሉ ግድያዎችና ጥቃቶች እንዲቆሙ የነገሌ ከተማና አካባቢው ነዋሪዎች ጠየቁ

55
ነገሌ ታህሳስ 5/2011 በአገሪቱ አንዳንድ ክፍሎች በዜጎች ላይ እየደረሱ ያሉት ግድያዎችና ጥቃቶች እንዲቆሙ በኦሮሚያ ክልል የነገሌ ከተማና አካባቢው ነዋሪዎች ዛሬ በሰላማዊ ሰልፍ ጠየቁ። በሰላማዊ  ሰልፉ ላይ ከታዩትና ከተሰሙት መፈክሮች መካከል ''የሕግ የበላይነት ይከበር! ''፣ ''የወሰን ችግር ይፈታ!''፣ ''በኦሮሞ ሕዝብ ላይ እየደረሰ ያለው ሞት፣ መፈናቀልና ስደት ይቁም!'' ይገኙበታል። ሰላማዊ ሰልፈኞቹ በተወሰኑ የአገሪቱ ክፍሎች እየተከሰቱ ያሉትን ሞት፣ ስደትና መፈናቀል እንዲያስቆሙ ለፌዴራልና ለኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥታት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። ከሰልፈኞቹ  መካከል አቶ ዋሪዎ ሳራ በሐረርጌ ፣ በወለጋ፣ በጉጂና ቦረና ዞን ሞያሌ አካባቢ በኦሮሞ ህዝብ ላይ እየደረሰ ያለው ሞትና መፈናቀል አሳሳቢ መሆኑን ተናግረዋል። መንግሥት የሕግ የበላይነትን በማስከበር እየጠፋ ያለውን ሕይወትና ንብረት ማስቆም ይገባዋል ብለዋል። በዝምታ የሚታለፍ ሁከትና ብጥብጥ ሕዝብን ለሞትና ስደት ከመዳረግ አልፎ፤ አገር ስለሚያፈርስ  በቸልታ እንዳይታይ አሳስበዋል። የለጋ ቡላ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ቃልቻ ቦሩ መንግሥት ችግሩን ለማስቆም የሕግ የበላይነት ከማስከበር ጎን ለጎን በብሄር/ብሄረሰቦች መካከል ውይይት ማድረግ ይገባዋል ይላሉ። የኦሮሞ ሕዝብ ከሌሎች ብሄር/ብሄረሰቦች ጋር ተቻችሎ ተከባብሮና ተረዳድቶ የሚኖርበት የመልካም ባህላዊ ሥርዓት ባለቤት በመሆኑ ችግሮችን ለመፍታት እንደማይቸገርም አስተያየት ሰጪው ገልጸዋል። ለዚህም መንግሥት ግጭቶችን በአገር ሽማግሌዎች፣ በገዳ ሥርዓትና በሌሎችም የዕርቀ ሰላም አማራጮች እንዲፈቱ  ሁኔታዎችን ማመቻቸት እንደሚገባው አመልክተዋል። የነገሌ ከተማ ከንቲባ አቶ ባሊ በዱ ለሰላማዊ ሰልፈኞቹ ባደረጉት ንገግር ግጭቶችን ለማስቆም የኦሮሞን ህዝብ አንድነት ትብብርና ሰላማዊ ትግል ይጠይቃል ብለዋል። መንግሥት የሕግ የበላይነትን ለማስከበርና ችግሮችን በውይይት ለመፍታት ከአገር ሽማግሌዎችና ከሃይማኖት አባቶች ጋር እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም