የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር ዘብ የአመራር አባላት አዲስ አበባ ገቡ

62
አዲስ አበባ ታህሳስ 5/2011 የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር ዘብ ሁለት የአመራር አባላት ዛሬ ረፋድ ላይ አዲስ አበባ ገቡ። የግንባሩ ሊቀመንበር አቶ ልዑል ቀስቅስ እና የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው አቶ ፀጋዬ መርጊያ ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የፕሮቶኮል ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄኔራል ምክትል ሹም አቶ ግስላ ሻውል ተቀብለዋቸዋል። ግንባሩ በኤርትራና በአውሮፓ ሲንቀሳቀስ የቆየ ሲሆን የአመራር አባላቱ ከጀርመን ፍራንክፈርት መምጣታቸውን ለማወቅ ተችሏል ። የግንባሩ ሊቀ መንበር አቶ ልዑል ቀስቅስ ለኢዜአ እንደተናገሩት ወደ አገር ቤት የገቡት በአገሪቱ የተጀመረውን ለውጥ ለመደገፍ ነው። አቶ ልዑል ከ11 ዓመታት ስደት በኋላ ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸውን ገልፀው "ስታገልለት የነበረው ለውጥ ፍሬ በማፍራቱ ወደ አገር ቤት ልገባ ችያለሁ" ብለዋል። በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ መሪነት የተጀመረው አገራዊ ለውጥ እገዛ የሚያሻው በመሆኑ "የለውጡ አካል ለመሆን ወደ ኢትዮጵያ መጥተናል" ሲሉም አክለዋል። የተጀመረውን አገራዊ ለውጥ ለመደገፍ ከመንግስት ጋር በትብብር እንደሚሰሩም ነው የገለጹት። የግንባሩ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ፀጋዬ መርጊያ በበኩላቸው ባለፉት ዓመታት የነበረው የፖለቲካ ሥርዓት አካታች ባለመሆኑ ከአገር መሰደዳቸውን ገልፀዋል። በአገሪቱ በተጀመረው አገራዊ ለውጥ በውጭ አገራት ሲታገሉ የቆዩ የበርካታ ፖለቲካ ፓርቲዎች የአመራር አባላት መግባት "ለውጡን ለመደገፍ ወደ አገር ቤት መግባት አለብኝ" የሚል ስሜት እንዳሳደረባቸውም ተናግረዋል። በመሆኑም በመንግስት የተጀመሩ የለውጥ እርምጃዎችን እንደሚደግፉ አስታውቀዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም