በሙስና ወንጀል በተጠረጠሩ የቀድሞ የሜቴክ አመራሮች ላይ የተጨማሪ ምርመራ ጊዜ ተጠየቀ

60
አዲስ አበባ ታህሳስ  4/2011 የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በብርጋዴር ጀኔራል ጠና ቁርንዲ መዝገብ በሙስና ወንጀል በተጠረጠሩ የብረታ ብረት እና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) የቀድሞ ስራ ኃላፊዎች ላይ የተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ጥያቄ ጉዳይ ለመወሰን ለአዳር  ለነገ  ከሰዓት ቀጠሮ ቀጠረ። በሙሰና ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር ከዋሉ ከ30 ቀናት ባላይ ያስቆጠሩት የቀድሞ የሜቴክ የስራ ሃላፊዎችና ሰራተኞች በፍርድ ቤቱ  10ኛ ወንጀል ችሎት ቀርበው የተጨማሪ 14 ቀናት የምርመራ ጊዜ ተጠይቆባቸዋል። ፖሊስ ከዚህ በፊት በተሰጠው የጊዜ ቀጠሮ በእያንዳንዱ ተጠርጣሪ ላይ የሰራቸውን ተግባራት ገልጾ፣ ከወንጀሉ ክብደትና ውስብስብነት የሰውና የሰነድ ማስረጃ ለማሳሰባበብና ሌሎች ቀሪ ስራዎችን ለማከናወን የጊዜ ቀጠሮ ያስፈልገኛል ብሏል። የተጠርጣሪ ጠበቆች በበኩላቸው መርማሪ ፖሊስ 26 ተጠርጣሪዎችን በአንድ መዘግብ ተጨፍልቆ ተጨማሪ ጊዜ መጠየቁ አግባብነት የለውም፣ ከዚህ በፊት በተፈቀደለት ጊዜም በቂ ስራ አልሰራም፣ ተጠርጣሪዎች ከመንግስት ተቋማት የሚሹ ሰነዶችን ለማሸሽ እድልና አቅም የላቸውም በማለት ተከራክረዋል። ከተጠርጣሪዎች የቀድሞ አገራዊ አስተዋጽኦ፣ መልካም ጸባይ፣ የጤንነት ሁኔታ፣ የቤተሰብና ተያያዥ ግላዊ ምክንያቶችን በማንሳትም የዋስትና መብታቸው ተከብሮ ጉዳያቸውን በውጭ ሆነው እንዲከታታሉም ጠይቀዋል። በተናጠል የደንበኞቻቸውን የጥርጣሬ ድርጊት በማንሳትም "ከባድ የሙስና ወንጀል ያስብላል ወይ" ከሚሉ ጥያቄዎች ጀምሮ የመርማሪ ፖሊስ ምክንያቶችን በማንሳት ተከራክረዋል። መርማሪ ፖሊስ በበኩሉ ተጠርጣሪዎች ምስክር ያባብላሉ፣ ማስረጃ ያጠፋሉ፣ ይሰወራሉ፣ በሙስና ያገኙትን ሃብት ያሸሻሉ በሚል የዋስትና ጥያቄውን ተቃውሟል። ችሎቱም የመደበኛ ጊዜው በመጠናቀቁ የአመልካችና የጠበቃ ቀሪ ክርክሮችን ሰምቶ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜው ይፍቀድ፤ አይፈቀድ በሚለው ላይ ውሳኔ ለመስጠት ለአዳር ለነገ ከሰዓት ቀጠሮ ሰጥቷል። በሌላ በኩል በሙስና ወንጀል ተጠርጣሪዎች የሮቬራ ሆቴል ባለቤት አቶ ዓለምፍፁም ገብረ ስላሴና የቀደሞው የኢትዮ-ቴሌኮም ሴኪዩሪቲ ዲቪዥን ሃላፊ ኮለኔል ጉደታ ኦላናን  ጉዳይ ለማየት ለነገ ጥዋት ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል። በተመሳሳይ በቀድሞው የኢትዮ-ቴሌኮም ከፍተኛ የስራ ኃላፊ በነበሩት በአቶ ኢሳያስ ዳኘውና የሰብአዊ መብት ጥሰት ተጠርጣሪዎቹ ረዳት ሳጅን ኪዳኔ አሰፋና አቶ ሳሙኤል ግዲሳ ጉዳይን ለማየት ለነገ ከሰዓት ቀጠሮ ሰጥቷል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም