የአካባቢያቸውን ሰላምን በመጠበቅ ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ የድሬዳዋ ነዋሪዎች ገለጹ

588

ድሬደዋ ታህሳስ 4/2011 የአካባቢያቸውን ሰላም ተቀናጅተው በመጠበቅና ችግር የሚፈጥሩትን ለህግ በማቅረብ ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ የድሬዳዋ አስተዳደር ነዋሪዎች ገለጹ፡፡

ከድሬደዋ አስተዳደር የተወጣጡ ከ3 ሺህ በላይ ነዋሪዎች ካለፈው ሣምንት ጀምሮ ሲያካሄዱ የቆዩት የሰላም ኮንፍረንስ  ዛሬ አጠናቀዋል፡፡

ከኮንፍረንሱ ተሳታፊዎች መካከል ወጣት ኪሩቤል ዘርፉ እንዳለው ወጣቱም ሆኑ ሌሎች ነዋሪዎች ለሰላም መስፈን ኃላፊነታቸውን እየተወጡ ነው፡፡

ህዝቡን የሚመራው አካል ለሰላም መስፈን በቁርጠኝነት ሊሰራና የህብረተሰቡን በተለይም የወጣቱን የሥራ ጥያቄና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ሊፈታ እንደሚገባም አመልክቷል፡፡

ድምጻዊት  መቅደስ ንጋቱ በበኩሏ ” ሰላም እንደምተነፍሰው አየር ያስፈልገናል፤ ለሰላም መከበር ደግሞ ሁሉም የድሬዳዋ ነዋሪዎች በብሔር ፣በቋንቋና በኃይማኖት ሳይለያዩ ተቀናጅተው መስራት አለባቸው “ብላለች፡፡

በሙያዋ የታዋቂው የመሐሙድ አህመድን “ሰላም” ዘፈንን ባገኘችው መድረክ በማቀንቀን ስለ ሰላም አስፈላጊነት ለታዳጊ ወጣቶች እንደምታስተምርም ተናግራለች፡፡

የድሬዳዋ ነዋሪዎች በኃይማኖት ፣ በሐዘንና በደስታ የማይለያዩ ህዝቦች በመሆናቸው ይህንን መገለጫችንን እያደፈረሱ የሚገኙት አካላትን በመመከት ለህግ በማቅረብ የድርሻቸውን እንደሚወጡ የገለጹት ደግሞ ሌላዋ የኮንፍረንሱ ተሳታፊ ወይዘሮ  ዘይቱና አሊ ናቸው፡፡

የሀገር ሽማግሌ የሆኑት መሐመድ ጅብሪል በበኩላቸው  አንዳንድ የሀገር ሽማግሌዎችና የኃይማኖት አባቶች ራሳቸውን ከፖለቲካ መስመር በማራቅ ወጣቶችን በፍቅር በማስተሳሰር ለአካባቢያቸው ሰላምና ልማት ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

” ሽምግልናና የእምነት አባት ከፈጣሪና ከህዝብ የሚሰጥ ፀጋ ነው፤ ይህ በጊዚያዊ የአበል ጥቅም ሊለወጥ አይገባም” ብለዋል፡፡

አቶ ከድር አባስ የተባሉት ነዋሪ በሰጡት አስተያየት ለሰላም መከበር ከትልቅ እስከ ትንሽ ተቀናጅቶ በመስራት ችግር ፈጣሪዎችን ስርዓት ማሲያዝ እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡

” በመንግስት ተቋማት ውስጥ ተሸሽገው በህዝቡ ውስጥ ችግር የሚፈጥሩ አንዳንድ አመራሮች አሉ ፤እነዚህን ማጋለጥና ለህግ ማቅረብ አለብን” ብለዋል፡፡

የሰላም ኮንፍረንስ   ለነዋሪው መዘጋጀቱ ተገቢና አስፈላጊ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ ወይዘሮ  ፍሬወይኒ ሰመረ ናቸው፡፡

አስተያየት ሰጪዋ እንዳሉት ኮንፍረንሱ የነዋሪዎችን የርስ በርስ መተማመንን በመመለስ ሁሉም በሙሉ አቅሙ ለአካባቢው ሰላም ተቀናጅቶ እንዲሰራ ያስችላል ፡፡

ሊቀብርሃናት ቀለመወርቅ ቢምረው በበኩላቸው ድሬዳዋ  ቀድሞ የገነባቸው የሰላም፣ የአንድነት፣ የፍቅር እሴቶችን በመመለስ አሁን የጀመረችውን ዕድገቷን ማስቀጠል እንደሚገባ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የሰላም ኮንፍረንሱም ማጠቃለያ ውይይት የመሩት የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ኢብራሂም ዑስማን “ከሚቀጥለው ሣምንት ጀምሮ ህዝብን ለመልካም አስተዳደር ችግሮችና ለሰላም መደፍረስ አስተዋጽኦ ያደረጉ  አመራሮችን በአዲስ የመተካት ሥራ ይካሄዳል” ብለዋል፡፡

እንደከንቲባው ገለጻ ወጣቱ በተደጋጋሚ ላቀረባቸው የሥራ እድል  ጥያቄ ትርጉም ባለው መንገድ ምላሽ ለመስጠት  በየሴክተሩ፣ በጥቃቅንና አነስተኛ እንዲሁም በግዝፍ የልማት ፕሮጀክቶች ላይ ተጠቃሚ የማድረግ ስራ እየተሰራ ነው፡፡

የወጣቱም ሆነ የህዝቡ ጥያቄዎች ለመመለስ የሚደረገው ጥረት እንዲሳካ ሁሉም ነዋሪ ለሰላም መከበር እያከናወነ የሚገኘውን ተግባር እንዲያጠናክርም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በሰላም ጉባኤው የተሳተፉት ነዋሪዎች  ባወጡት የጋራ የአቋም መግለጫ ብሔርን ሽፋን በማድረግ ህዝብን  ለማጋጨት የሚደረጉ ጥረቶች አጥብቀው እንደሚቃወሙ አስታውቀዋል፡፡

የግለሰቦችን ፀብ ወደ ቡድን ፣ሰፈር አልፎም ወደ ብሔር ለመውሰድ የሚደረግን ጥረት ማንንም የማይወክልና ተቀባይነት የሌለው መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ለሰላም መደፍረስ ምክንያት ለሚሆኑ የስራ እጥነትና የመልካም አስተዳደር ችግሮቻቸው መፍትሄ መስጠት እንደሚገባ ነዋሪዎቹ በአቋም መግለጫው ላይ አመልክተዋል፡፡