በሰሜን ሸዋ የደን ሽፋንን ለማሳደግ የዛፍ ችግኝ ዝግጅት እየተካሄደ ነው

89
ደብረብርሃን ታህሳስ 4/2011 በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን  የደን ሽፋንን ለማሳደግ የዛፍ ችግኝ ዝግጅትና ቀደም ብለው የተተከሉትን የመንከባከብ ስራ እየተካሄደ መሆኑ የዞኑ ግብርና መምሪያ ገለጸ፡፡ በዚህም ስራ በተያዘው ዓመት  የዞኑን  የደን  ሽፋን   16 ነጥብ 2 በመቶ ለማድረስ  ነው፡፡ በመምሪያው  የደን አግሮ ፎረስተሪ ባለሙያ አቶ በላይ ግርማ ለኢዜአ እንዳሉት በመጪው  የክረምት ወቅት   59ሺህ 250 ሄክታር አዲስ መሬት ላይ ኢኮኖሚያዊ ጠቄሜታ ያላቸው  የዛፍ ችግኞች እንዲለሙ ይደረጋል፡፡ አሁን ላይ የግል፣ የመንግስትና  የማህበራት ይዞታ በሆኑ 49ሺህ 966 የችግኝ ማፍያ ጣቢያዎች  ከግማሽ ቢሊዮን  በላይ ችግኞች  ለማዘጋጀት እየተሰራ ነው፡፡ ከሚዘጋጀቱ ችግኞች መካከል ባህር ዛፍ ፣   ግራር ፣ ዋናዛ ፣ ወይራ ፣ኮሶ እና ብርብራ  ይገኙበታል፡፡ 20 ኩንታል የደን ዘር እና የችግኝ ማፍያ ፕላስቲክ ተገዝቶ ጥቅም ላይ እየዋለ  ነው፡፡ እንደባለሙያው ገለጻ  በአርሶ አደሮች ተሳትፎ   በ2009ዓ.ም.  በ25ሺህ 34ሄክታር መሬት ላይ  ከ212 ሚሊየን  በላይ ችግኞች  ተተክለዋል፡፡ ከተተከለው ውስጥም  ከ162ሚሊየን በላይ መጽደቁን ባለሙያው አመልክተው እስካለፈው ዓመት በዞኑ የለማው  ደን ስፋት 246ሺህ 450ሄክታር መሬት እንደሚሸፍን አስረድተዋል፡፡ ይህም ሽፋን 15 ነጥብ 2 በመቶ መሆኑና  በተያዘው ዓመት ደግሞ  አንድ በመቶ ለመጨመር ቀደም ብሎ ተተክለው የጸደቁትን  በመንከባከብ ጭምር እየተሰራ ነው ተብሏል፡፡ አርሶ አደር ግዛው  ዓለሙ በመንዝ ማማ ምድር ወረዳ የቀበሌ ሁለት ነዋሪ ሲሆኑ ዛፍን አለአግባብ  በመጨፍጨፉ  የአካባቢያቸው  ሙቀት እየጨመረ  ለኑሮቸው አስቸጋሪ ሆኖባቸው መቆየቱን ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት ገልጸዋል፡፡ አርሶ አደሩ እንዳሉት ደን አለአግባብ መጨፍጨፍ እና በምትኩ ያለመትከል የሚያስከትለውን ጫና ከባለሙያዎች በመረዳታቸው   በግልና በጋራ የዛፍ ችግኞችን እየተከሉ በመንከባከብ   የማሳደግ ልምዳቸው  ተሻሽሏል፡፡ ከአምስት ዓመት በፊት በተራቆተ ሁለት  ሄክታር የግል መሬታቸው ላይ 3ሺህ የባህርዛፍ ችግኝ ተክለው  እያለሙ  በመሸጥ  ባለፈው ዓመት ብቻ  80ሺህ ብር ገቢ ማግኘታቸውን  ጠቁመዋል፡፡ በተያዘው  ዓመትም የደን ችግኝ አፍልተው  በመትከልና በመንከባከብ  የአየር ንብረት ለውጡን ለመከላከል እየሰሩ እንደሚገኙ  አርሶ አደሩ አስረድተዋል፡፡ በደብረብርሃን  ከተማ የዛንዝራ ንዑስ ቀበሌ ነዋሪ ወጣት መለሰ ተሾመ  በበኩሉ ከጓደኞቹ ጋር  እድገት በጋራ ደን ልማት ማህበር  በሚል ስያሜ አቋቁመው  የባህር ዛፍ ችግኝ  እያለሙ በመሸጥ ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ዘንድሮ ብቻ  በግሉ  ከባህር ዘፍ ችግኝ ሽያጭ  25ሺህ ብር  ገቢ ማግኘቱን ጠቁመዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም