በኢትዮጵያ ሁሉን አቀፍ የጤና ሽፋን ፍትሀዊ ና ጥራት ያለው እንዲሆን የባለድርሻዎች ቅንጅት ያስፈልጋል

134
አዲስ አበባ ታህሳስ 3/2011 በኢትዮጵያ ሁሉን አቀፍ የጤና ሽፋን ፍትሀዊ ተጠቃሚነትን ያረጋገጠና ጥራት ያለው እንዲሆን ከባለድርሻ አካላት ጋር ያለው ቅንጅት የበለጠ መጠናከር እንዳለበት ተገለፀ። በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሁለተኛ ጊዜ፤ በኢትዮጵያ ደግሞ ለመጀመሪያ ጊዜ ዛሬ ታስቦ የዋለውን "ሁሉን አቀፍ የጤና ተደራሽነት ቀን" አስመልክቶ በጤና ­ጥበቃ ሚኒስቴር መግለጫ ተሰጥቷል። "በተባበረ ክንድ የሁሉን አቀፍ ጤና ተደራሽነትን እናረጋግጥ" በሚል መሪ ሃሳብ ዘንደሮ ቀኑ የተከበረው። በየዓመቱ ታህሳስ ሶስት ቀን "ሁሉን አቀፍ የጤና ተደራሽነት ቀን" ተብሎ እንዲከበር የተወሰነው በተባበሩት መንግስታት ድርጅት አማካኝነት ነው። ዓላማውም ጥራት ያለው ሁሉን አቀፍ የጤና አገልግሎትን እ.አ.አ እስከ 2030 በመላው ዓለም ለማዳረስ የተገባውን ዓለም አቀፍ ቃል እውን ማድረግ እንዲቻል ነው። "ሁሉን አቀፍ የጤና ተደራሽነት ማረጋገጥ  የሚቻለው በየትኛውም ቦታና የምጣኔ ኃብት ደረጃ ላይ የሚገኝ ሰው የገንዘብ ችግር እክል ሳይሆንበት ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት ማግኘት ሲችል ነው" ሲሉ በጤና ሚኒስቴር የሚኒስትሩ ፅህፈት ቤት ዳይሬክተር ጄኔራል ዶክተር አሸናፊ ቤዛ ተናግረዋል። ይህንን እውን ማድረግ ይቻል ዘንድም ኢትዮጵያ የተለያዩ የጤና ልማት ሥራዎችን እያከናወነች መሆኑንም ጠቅሰዋል። ሁለንተናዊ የጤና ሽፋንን ማረጋገጥ የአገሪቱ የጤና ፖሊሲ እሴቶችና መርሆዎች ምሶሶ አድርጎ ማስቀመጡን የገለፁት ዶክተር አሸናፊ የጤናው ዘርፍ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ትኩረቶችም በዚሁ መሰረት የተቃኙ መሆናቸውን አብራርተዋል። ሁለንተናዊ የጤና ሽፋን የማረጋገጡ ተግባር በወረዳ ደረጃ ጭምር ትኩረት ተሰጥቶት እየተከናወነ ነውም ብለዋል። ሆኖም በጤናው ዘርፍ ያለው የፋይናንስ ውስንነት እንዲሁም በከተማና በገጠር መካከል ያለው ከፍተኛ የጤና አገልግሎት ሽፋን ልዩነት ለሁለንተናዊ የጤና ሽፋን መሳካት ማነቆ እንደሆኑም አብራርተዋል። እየገጠሙ ያሉ ችግሮችን ለመፍታትም ኀብረተሰቡ ራሱን ከበሽታ መጠበቅና የማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎት አባል በመሆን ራሱን ከአቅም በላይ ከሆነ የጤና ወጪ መጠበቅ እንደሚኖርበት ገልፀዋል። በኢትዮጵያ ሁሉን አቀፍ የጤና ሽፋንን አስከ 2022 ዓ.ም ለማሳካት ጠንካራና ፍትሃዊ የጤና ስርዓትን ለመገንባት የጋራ ጥረትና ተጨባጭ እርምጃ ያስፈልጋል ያሉት ዶክተር አሸናፊ የባለድርሻ አካላት ተሳትፎም ሊጠናከር እንደሚገባ ነው ያብራሩት። ቀኑ መከበሩም የተጀመሩ ስራዎችን ለማጠናከርና የኀብረተሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግ እንደሚረዳ ነው የተናገሩት። በኢትዮጵያ ሁሉን አቀፍ የጤና አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ ባለፉት 15 ዓመታት በተከናወኑ ተግባራት የጤና ሽፋን ከ95 በመቶ በላይ መድረሱን የተናገሩት ደግሞ የአለም አቀፍ መሰረታዊ የጤና እንክብካቤ ኢንስቲትዩት በኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ኤፍሬም ተክሌ ናቸው። ሆኖም ፍትሀዊ ተጠቃሚነትና ጥራትን ማሻሻል ላይ ተጨማሪ ሥራዎች የሚያስፈልጉ በመሆኑ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ገልፀዋል። በተለይ ከሰሀራ በታች የአፍሪካ አገራት የጤና አገልግሎት ሽፋን ዝቅተኛ በመሆኑና የዓለም መንግስታትን ለማነቃቃት ሁሉን አቀፍ የጤና ተደራሽነት ቀን መከበር መጀመሩን ተናግረዋል። የአለም መንግስታት መሰረታዊ የጤና አገልግሎትን ለማዳረስ ከ40 ዓመት በፊት ስምምነት ላይ ቢደርሱም እ.አ.አ በ2000 ጤናን ለሁሉም በታሰበው ልክ ማዳረስ ባለመቻሉ የምዕተ ዓመትና ዘላቂ የልማት ግቦች መቀረፃቸውን አብራርተዋል። በአሁኑ ወቅትም እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገራት ከተደራሽነት አንፃር የመጡ ለውጦች መኖራቸውን ገልፀዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም