ዩኒቨርሲቲዎች በተጽዕኖ የሚፈጠርባቸውን አለመረጋጋት በራስ አቅም ለማስወገድ ትኩረት እንዲሰጡ ተጠየቀ

104
አዲስ አበባ ታህሳስ 3/2011 የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በውጫዊ ተጽዕኖ የሚፈጠርባቸውን አለመረጋጋት በራስ አቅም ለማስወገድ ትኩረት እንዲሰጡ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጥሪ አቀረቡ። የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከማህበረሰቡ ጋር ጠንካራና ተጽዕኖው አዎንታዊ የሆነ መስተጋብር መፍጠር እንዳለባቸውም አሳስበዋል። አቶ ደመቀ ይህን ያሉት ዛሬ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን የመማር ማስተማር ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክቶ በተካሄደ የባለድርሻ አካላት ውይይት ላይ ነው። የሳይንስና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት ወልደማርያምን ጨምሮ የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዚዳንቶች፣ የቦርድ ሰብሳቢዎችና ባለድርሻ አካላት በውይይቱ ተሳትፈዋል። በመድረኩ ከመንግስት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች የተውጣጡ ቡድኖች ወደተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች አቅንተው የሰበሰቡትን ግብዓት የሚያመላከት ሪፖርት ቀርቦ ምክክር ተደርጎበታል። በሪፖርቱ የምዘና ስርዓት ከቦታ ቦታ መለያየት፣ የፈጣን ምላሽ እጦት፣ በግቢ ውስጥ የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች መኖር፣ የተማሪዎች አመዳደብ ስብጥር አለመኖር በዩኒቨርሲቲዎች ከሚታዩ ግጭት አባባሽ ሁኔታዎች መካከል ተጠቅሰዋል። ሌሎች በሰላማዊ የመማር ማስተማር ስራ ላይ እክል የሚፈጥሩ ጉዳዮችም ከተሳታፊዎች ተነስተዋል። ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ለተነሱ ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ 'ያለንበት ወቅት ከመቼውም ጊዜ በላይ የህብረተሰብ ንቅናቄ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ላይ መጠናከር እንዳለበት ያሳያል' ብለዋል። በሁለቱ መካከል ጠንካራና ተጽእኖው አዎንታዊ የሆነ መስተጋብር እንደሚያስፈልግ ጠቁመው ዩኒቨርሲቲዎች ውጫዊውን ተጽእኖ ለመቀየር "እኔ ምን ሰራሁ" ሲሉ ራሳቸውን እንዲጠይቁ አሳስበዋል። ዩኒቨርሲቲዎች የኢትዮጵያ ማሳያ በመሆናቸው በተማሪዎች መካካል ጠንካራ የባህል ልውውጥ እንዲኖር የሚያስችሉ ሁኔታዎች መመቻቸት እንዳለበትም ጠቁመዋል። የሳይንስና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሚኒስትሯ ዶክተር ሂሩት ወልደማርያም በበኩላቸው መስሪያ ቤታቸው በዩኒቨርሲቲዎች ላይ እውቀትና ብዝሃነትን ያማከለ የአመራር፣ የመምህራን ቅጥርና የተማሪ ቅበላ እንዲኖር እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል። በተማሪዎች ዘንድ ተቀባይነት ያላቸው ግለሰቦች በዩኒቨርሲቲዎች ቀጣይነት ያለው የማነቃቂያ ንግግር የሚያደርጉበትን ሁኔታ የሚያመቻች መመሪያ መውጣቱንም አክለዋል። አንዳንድ ዩኒቨርሲቲዎች ይህን መመሪያ ገቢራዊ ማድረግ መጀመራቸውን በመጠቆም። ሚኒስቴሩ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ግጭት የሚያባብሱ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለማስወገድ የሚያደርጉትን ጥረት በቅርበት እንደሚደግፍም ቃል ገብተዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም