“ግፍ ፈፃሚዎችን ሀገራዊ ወሰንና ዓለም አቀፋዊ ድንበር ሳይገድበን ለሕግ እናቀርባለን”-ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ

5898

ታህሳስ 3/2011 ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ግፍ ፈፃሚዎች ከየትኛውም ብሔር ገብተው ይደበቁ የትኛውም ወገን ይጩህላቸው በወንጀል እስከተጠረጠሩ ድረስ ካሉበት አድነን ለሕግ እናቀርባለን ብለዋል።

ሀገራዊ ወሰንም ሆነ ዓለም አቀፋዊ ድንበር ወንጀለኞችን ለፍርድ ከመቅረብ አይታደጋቸውም ያሉት ዶክተር ዐብይ፣ መንግስት ቁርጠኛ መሆኑን ነው የጠቀሱት።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት በሰብአዊ መብት አያያዝ ዙሪያ ዛሬ ባስተላለፉት መልዕክት ነው።

የኢትዮጵያ ሕዝብ ሁልጊዜ አምባገነናዊ ሥርዓትን ለመገርሰስ ሲታገል የኖረውና መሥዋዕት የሆነው ግፍ እንዲቆም ፍትሕ እንዲሰፍን እንጂ ሌሎች ግፈኞችን ለመተካት አይደለም ብለዋል።

በሕዝብ ትግል ሥልጣን ላይ የወጡ አካላት ከራሳቸው ፍላጎት ውጪ የሕዝብን ፍላጎት ማሟላት አልቻሉም ነው ያሉት።

በተለይ የዴሞክራሲ ምህዳሩ እየጠበበ፣ ዜጎች በብሔራቸውና በያዙት የፖለቲካ አስተሳሰብ የሚደርስባቸው በደል እየከፋ፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰቱ እየባሰ ሙስናው ሀገሪቱን እስከ አንገቷ እየዋጣት መምጣቱን በመግለጫቸው ተናግረዋል።

ሕዝቡን ′እንደ አንድ ልብ መካሪ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ′ “በደልና ግፍ በቃን” ብሎ እንዲነሳ ያደረጉትም እነዚህ መከራዎች ናቸው ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ።

በሀብት፣ በንብረትና በፖለቲካ ተሳትፎ ከሚሰራው ግፍ በባሰ ሰብዓዊ መብት ላይ የሚሰራው ግፍ ዜጎች መፈጠራቸውን እንዲጠሉ ማድረጉን ገልጸዋል።

በፖሊስ፣ በደህንነት፣ በፍርድ ቤቶች፣ በማረሚያ ቤቶችና በሌሎች የመንግስት ሃላፊነት በሚገኙ ባለስልጣናት ፈቃጅነትና መሪነት ህሊናቸውን ሽጠው ለሆዳቸው ባደሩ የግፍ ሰራዊት ተላላኪነት በዜጎች ላይ ከባድ ሰቆቃ መድረሱን በመልዕክታቸው አንስተዋል።

ግፍ ፈጻሚዎቹ ከሳሽም፣ ምስክርም፣ መርማሪም፣ አሣሪም ፣ዓቃቤ ህግም፣ ዳኛም ሆነው የግፉን ድራማ መተወናቸውን በመልዕክታቸው አስፍረዋል።

አብዛኛው ኢትዮጵያዊ  ሃይማኖተኛ እና ለሞራላዊ ድንጋጌዎች ከፍተኛ ቦታ የሚሰጥ ቢሆንም ግፈኞቹ ግን ከሰውነት ተራ መውጣታቸው በፈጸሟቸው ግፎች አሳይተዋል ነው ያሉት።

መንግሥት ግፍ ፈፃሚዎች ዋጋቸውን በሕግ እንዲያገኙ የሚሰራ ሲሆን የተፈፀሙ ግፎች በቀጣዩ ትውልድ ላይ እንዳይፈፀሙ አስተማማኝ ስርዓት እንዲዘረጋ ይሰራል ብለዋል።

ከዚያ ባሻገር አሁን ያለው ሁሉም አካል ከግፍ ፈፃሚዎቹ የተሻለ ሆኖ መገኘትና በተግባር ማሳየት እንደሚገባም ጠቁመዋል።

ግፍ ፈፃሚዎቹ በሰላም ተኝተው እንዲያድሩ መፍቀድ የለብንም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ በህግ ቅጣት አግኝተው ተተኪው ትውልድ ትምህርት፣ ተጎጂዎች የህሊና እረፍት እንዲያገኙ መስራት አለብን ነው ያሉት።

በሌላ በኩል የግፈኞቹን አረመኔያዊ ድርጊት ፈጽሞ መድገም እንደማይገባ አሳስበው ህጎችን ማሻሻል፣ አሰራሮችን ማስተካከል፣ ተቋማትን ማብቃት፣ የዝርፊያና የአምባገነንነት በሮችን መዝጋት እንደሚገባ ጠቅሰዋል።

ለዚህም አሁን እየተከናወኑ የሚገኙ የለውጥ ስራዎችን አጠናክሮ በማስቀጠል ኢትዮጵያ ውስጥ የዜጎችን ዴሞክራሲያዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ሰብዓዊና ፖለቲካዊ መብቶችን በሚገባ የሚያከብርና የሚያስከብር ስርዓት መገንባት ይኖርብናል ነው ያሉት።

በፍርድ ቤቶች፣ በምርጫ ቦርድ፣ በሚዲያዎች፣ በመከላከያና ደህንነት፣ በፖሊስና በማረሚያ ቤቶች እየተወሰዱ ያሉ ማሻሻያዎች ዓላማቸው ዘላቂ ስርዓት እውን ማድረግ እንደሆነ ነው የጠቀሱት።

በቀጣይም በሌሎች ተቋማት ላይ የማሻሻያ ስራዎች እንደሚተገበሩም ጠቁመዋል።

ግፈኞች በጭፍን አዕምሮ በወገናቸው ላይ የፈፀሙት ግፍ ለበቀል እንዳያነሳሳን መጠንቀቅ፣ ጥላቻቸውን አለመውረስ፣ህግን አክባሪና ፈጣሪን ፈሪ መሆን ያስፈልጋል ነው ያሉት።

ግፈኞች ከየትኛውም ብሔር ይውጡ እነሱ ባጠፉት ምክንያት ጣት የሚቀሰርበት ብሔር አይኖርም፤ ወንጀለኞችን ነጥሎ ለፍርድ ማቅረብ ይገባል ሲሉም ተናግረዋል።

“ወንጀለኞች ማንም ይሁኑ ማን፣ ከየትኛውም ብሔር ገብተው ይደበቁ የትኛውም ወገን ይጩህላቸው በወንጀል እስከተጠረጠሩ ድረስ ካሉበት አድነን ለሕግ ማቅረባችን አይቀሬ ነው” ብለዋል።

ሀገራዊ ወሰንም ሆነ ዓለም አቀፋዊ ድንበር ወንጀለኞችን ለፍርድ ከመቅረብ አይታደጋቸውም ያሉት ዶክተር ዐብይ፥ መንግስት ለዚህ ቁርጠኛ መሆኑን ነው ያነሱት።

ዘላቂና በጊዜ ሂደት የማይቀያየሩ፣ ሰቆቃን የሚያስቀሩ፣ ለግለሰቦች ፍላጎት የማይገዙ በሁላችንም ፍላጎት ላይ የተመሰረቱ ተቋማትን ለመገንባት መረባረብ ይገባል ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።