በአገሪቱ የሚስተዋሉ የጸጥታ ችግርና ስጋት እንዲወገድ ኢትዮጵያውያን ያለ ምንም ልዩነት እንዲሰሩ ተጠየቀ

78
ሐዋሳ ታህሳስ 3/2011 በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች እየተስተዋለ ያለው የጸጥታ ችግርና ስጋት እንዲወገድ ኢትዮጵያውያን ያለ ምንም ልዩነት እንዲሰሩ የሰላም አምሳደሮች ጠየቁ። ከዘጠኝ ክልሎችና ሁለት ከተሞች አስተዳደሮች የተውጣጡ ሴት የሰላም አምባሳደሮች ቡድን በደቡብ ክልል ሀላባና ሐዋሳ ከተሞች በመገኘት ከኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር ተወያይተዋል፡፡ የቡድኑ መሪ በሰላም ሚኒስቴር የሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ዳይሬክተር ወይዘሮ አበባ ተገኝ በሀላባ ከተማ ከደቡብ ክልል ሴቶች ማህበር አመራሮች ጋር በተደረገው ውይይት ላይ እንዳመለከቱት ኢትዮጵያውያን በዘር፣ በሃይማኖትና በብሄር ሳይከፋፈሉ  ከችግሮቻቸው ለመውጣት በጋራ መነሳት ይጠበቅባቸዋል። ሰላም ለአገር ልማትና ዕድገት ወሳኝና ቁልፍ መሣሪያ  መሆኑን አመልክተው ሁከትና ግርግር በሚከሰትባቸው አካባቢዎች ከማንም በላይ ተጎጂ የሚሆኑትን ሴቶች ከጉዳት ለመጠበቅ በትኩረት ሊሰራ ይገባል ብለዋል፡፡ ወንዶች ከማንም በላይ የእናታቸውንና የባለቤቶቻቸውን ሐሳብ እንዲተገብሩ የጠየቁት ወይዘሮ አበባ፣ ሚኒስቴሩ ከሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ሚኒስቴር ጋር በመቀናጀት ያቋቋመው ቡድን በክልሎች እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በቡድኑ የሐረሪ ክልል ተወካይ ወይዘሮ ገነት አሰፋ እንዳሉት ሴቶች በጸጥታ እጦት ምክንያትም ጉዳት ሰለባ ከመናቸውም በላይ፤ለልጆቻቸውና ለባሎቻቸው ደህንነት በማሰብም በስጋት እንደሚኖሩ ተናግረዋል። ’’እኛ እናቶች ልጅ ወልዶ እስከማሳደግ ባለው ሂደት ለራሳችን ልብሳችንን እየሰፋን ለልጆቻችን አዲስ ገዝተን እያለበስን ከሰው በታች እንዳይሆኑብን ስናስተምር ኖረን መጨረሻ ላይ ግን ዩኒቨርሲቲ ሲሄዱ ሬሳቸው የሚመጣበት ሁኔታ ነው ያለው’’ ብለዋል፡፡ የደቡብ ኢትዮጵያ ሴቶች ማህበር ሊቀመንበር ወይዘሮ አስቴር ይርዳ እንዳሉት በሰላም እጦት ከማንም በላይ ተጎጂ የሚሆኑትን ሴቶች ለመታደግና  ቤተሰባቸውን ለመጠበቅ የሰላምን ጠቀሜታ ማስተማር እንደሚገባቸው አመልክተዋል፡፡ የሀላባ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ወይዘሮ ሂክማ ከይረዲን እንዳሉት ዞኑ ከሌሎች አካባቢዎች በአንጻራዊ ሁኔታ ሰላም የሚታይበት ቢሆንም፤ቀጣይነቱን ለማረጋገጥ የሐሳብ ልዩነቶችን በማቻቻል የአካባቢያቸውን ብሎም የአገሪቱን ሰላም ለማስጠበቅ ከሕዝቡ ጋር ተቀናጅተው እንደሚሰሩ አስታውቀዋል፡፡ በተመሳሳይ በሀዋሳ ከተማ በተደረገው ውይይት የከተማዋ የአገር ሽማግሌ አቶ ጥላሁን ቱቴ እንዳሉት የአገሪቱን ሰላም ለማደፍረስ የሚደረገው እንቅስቃሴ ሕዝብን መናቅ በመሆኑ ሊቆም ይገባዋል ብለዋል፡፡ ጥቂት ግለሰቦች በተለያዩ አካባቢዎች በሚያስነሱት ችግር እየደረሰ ያለውን ጉዳት ለማስቀረት የጋራ ጥረት ማድረግ እንደሚያስፈልግም  አመልክተዋል፡፡ ሌላው የአገር ሽማግሌ አቶ ቡኒሳ ቡልቡላ በበኩላቸው የነገዪቱ ኢትዮጵያ የዘር፣ የሃይማኖትና የጎሣ ልዩነት እንዳይኖርባት እንሰራለን ብለዋል፡፡ ቡድኑ ያስረከበውንን አደራ ተቀብለው ከቤተሰብ ጀምሮ በሰላም ጉዳይ ላይ የጋራ አቋም ለመያዝ እንደሚጥሩም ተናግረዋል፡፡ ቡድኑ 21 ሴቶች በአባልነት ያቀፈ ሲሆን፣እስካሁን በስምንት ክልሎች በመዘዋወር በሰላም ዙሪያ ከኅብረተሰቡ ጋር ተወያይቷል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም