የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተጠርጣሪዎች የሚዲያ ዘመቻ እንዲቆምላቸው ፍርድ ቤት ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው ጠየቁ

62
አዲስ አበባ ህዳር 3/2011 በሰብዓዊ መብት ጥሰት ተጠርጣሪዎች የሚዲያ ዘመቻ እንዲቆምላቸው ፍርድ ቤት ትዕዛዝ እንዲሰጥ ጠየቁ። ዛሬ በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 10ኛ ወንጀል ችሎት የቀረቡት በነጎሃ አጽብሀ መዝገብ ተጠርጣሪዎች ላይ ፖሊስ ያከናወናቸውን የምርመራ ስራ አቅርቦ ተጨማሪ 14 ቀናት የምርመራ ጊዜ ጠይቋል። ተጠርጣሪዎች በበኩላቸው ከተያዙ 32 ቀናት ቢሆንም ፖሊስ ቃል እንዳልተቀበላቸው ገልጸዋል። ''ፖሊስ በተሰጠው ጊዜ አዲስ ነገር አልሰራም፤ ስራውን እየሰራ አይደለም ያነሳቸው ምክንያቶች ተጨማሪ ጊዜ ቀጠሮ አያስጠይቅም'' ብለዋል። 33 ተጠርጣሪዎችን በአንድ መዝገብ አድርጎ መቅረቡ ችግር ስላለው ተለያይቶ እንዲቀርብ ተጠርጣሪዎችና ጠበቆቻቸው ለችሎት ጠይቀዋል። በእያንዳንዱ ተጠርጣሪ ላይ ዝርዝር የጥርጣሬ ድርጊት አልቀረበም ያሉት ጠበቆች ደንበኞቻቸው ቋሚ አድራሻና ማንነት ያላቸው ስለሆኑ የማይሰወሩ ናቸው በማለት ዋስትና እንዲፈቀድ ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል። እንዲሁም በአዲስ አበባ ፖሊስ የታሰሩት ተጠርጣሪዎች በመስከረም ወር ድጋሚ ከታሰሩ ሌሎች እስረኞች ጋር በመታሰራቸው ህይወታቸውና ደህንነታቸው አስጊ ሁኔታ ላይ ስለሚገኝ አያያዛቸው እንዲታይላቸው ጠይቀዋል። ተጠርጣሪዎቹ ''በሚዲያ ዘመቻ ተከፍቶብናል፣ ወደፊት ነጻ ብንወጣ ከማህበረሰቡና ከቤተሰብ ጋር በተያያዘ ስነ ልቦናዊ ጉዳት ይኖረዋል፤ በፍትህ ሂደቱ ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል'' በማለት ለፍርድ ቤቱ ገልጸዋል። 'የፍትህ ሰቆቃ' በሚል ርዕስ በሚዲያዎች በተላለፈው ዘጋቢ ፊልም ላይ ስማቸው የተነሳው መርማሪ ፖሊስ ለችሎቱ ቅሬታቸውን አቅርበዋል። በእነጎሃ አጽብሀ መዝገብ 19ኛ ተጠርጣሪዋ የቀድሞ የወንጀል ምርመራ ቢሮ ባልደረባ ዋና ሳጅን እቴነሽ ''እኔ ባልያዝኩት የምርመራ መዝገብና ባልፈጸምኩት ድርጊት ሆን ተብሎ እኔን ለመጉዳት የተደረገ ድርጊት ነው'' ብለዋል። ባለፉት 10 ዓመታት ከስራቸው ጋር በተያያዘ ከማንም ጋር ያልተጣሉና በስራቸውም ምስጉን እንደሆኑ ገልጸዋል። በዘጋቢ ፊልሙ ላይ ስማቸውን ያነሳውን ግለሰብ ያልመረመሩት መሆናቸውንና በመልክም የማያውቁት መሆኑን ተናግረዋል። ''ሆን ተብሎ ፍርድ ቤቱንና ማህበረሰቡን ለማሳሳት የተደረገ ነው። ልጅ አለኝ ከወላድ ይህ ድርጊት አይፈጸምም'' ብለው የገለጹ ሲሆን አሁን በእስር ቤት ህጻን ልጃቸውን ይዘው ቀዝቃዛ ሲሚንቶ ላይ እያደሩ እንደሚገኙና ህጻን ለመመገብም ሆነ ለማጠብ እንደተቸገሩ ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል። ፍርድ ቤቱ በጉዳዩ ላይ ውሳኔ ለመስጠት ለይደር ቀጥሯል። በተመሳሳይ በሙስና ወንጀል የተጠረጠሩት የቀድሞ የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) አመራሮች ብርጋዴር ጄኔራል ጠና ቁርንዲን ጨምሮ ከሜቴክ ጋር በተያያዘ በሙስና ወንጀል የተጠረጠሩ 26 ሰዎች መደበኛ የችሎት ሰዓት በማለቁ ለአዳር ተቀጥረዋል። እንዲሁም በሙስና ወንጀል የተጠረጠሩት አቶ አለምፍጹም ገብረስላሴ በተመሳሳይ ለአዳር ተቀጥረዋል። ከዚህ ቀደም ፍርድ ቤቱ ለፖሊስ ለምርመራ በፈቀደው 14 ቀናት ጊዜ ውስጥ ፖሊስ ያከናወነው ስራ በጽሁፍ ለተጠርጣሪዎች ጠበቆች ተሰጥቶ ለነገ ተዘጋጅተው እንዲቀርቡ ትዕዛዝ ተሰጥቷል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም