ኢትዮጵያ ረሃብን ለማጥፋት ድህነትን የብሄራዊ ደህንነት ስጋቷ አድርጋ መውሰድ አለባት - የተባበሩት መንግስታት ድርጅት

134
አዲስ አበባ ታህሳስ 3/2011 ኢትዮጵያ በዘላቂ የልማት ግቦች በተስማማችው መሰረት ረሃብን ለማጥፋት ድህነትን የብሄራዊ ደህንነት ስጋቷ አድርጋ መውሰድ እንዳለባት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ገለጸ። የአገሪቱ ድህነትን ዜሮ ማድረግና ረሃብን መቀነስ ስትራቴጂ ግምገማ በመንግስታቱ ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አዳራሽ ተካሂዷል። በአሁኑ ወቅት በዓለም ላይ ከዘጠኝ ሰዎች አንዱ ወይም ከ815 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የተመጣጠነ ምግብ እንደማያገኙ የድርጅቱ መረጃ ያሳያል። በኢትዮጵያ ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እድገት እንዲሁም መሰረተ ልማት እየተስፋፋ ቢሆንም የአገሪቱ የድህነት ምጣኔ 23 በመቶ ላይ ነው። እንደ አውሮፓዊያኑ የዘመን ቀመር 2018 ብቻ ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ከ350 ሺህ በላይ ህጻናት በከፋ ድህነት ውስጥ ይገኛሉ። በአገሪቱ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ያለባቸው 3 ነጥብ 48 ሚሊዮን ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ህጻናትና ሴቶች ሲገኙ፤ 15 ሚሊዮን ዜጎችም ህይወታቸውን በእርዳታ ይገፋሉ። በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ተጠሪ ኤንያስ ቹማ እንዳሉት አገሪቱ በ2030 የዘላቂ የልማት ግቦች ረሃብን ለማጥፋት የገባችውን ቃል ለመፈጸም ከባድ ስራ ይጠብቃታል። ከ25 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ዜጎቿ በድህነት ውስጥ በመሆናቸው ድህነትና ረሃብን ጨርሶ የማጥፋት ስትራቴጂን የብሄራዊ ደህንነቷ አካል አድርጋ መውሰድ ይኖርባታል ብለዋል። ኢትዮጵያ በ2025 መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ ለመሰለፍና አጀንዳ 2063ን ለማሳካት ለድህነት ቅነሳ ቅድሚያ መስጠት አለባት ብለዋል። ድህነትን ዜሮ የማድረግና ረሃብን መቀነስ ስትራቴጂ ግምገማ ለኢትዮጵያ መልካም ልምድ መሆኑን የገለጹት ኤንያስ ቹማ በቀጣይ በገቢ አሰባሰብ፣ በቴክኖሎጂ ሽግግር፣ በአቅም ግንባታና በተቋማዊ ትብብር ላይ እንድታተኩር ጠቁመዋል። የምክክር ጥናትና ትብብር ማዕከል ከፍተኛ አማካሪ አምባሳደር ተፈራ ሻውልም ኢትዮጵያ ረሃብን ለማጥፋት የዜጎችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አቅም ማሳደግ እንዳለባት ተናግረዋል። በኢትዮጵያ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች በድህነት ውስጥ የሚሰቃዩ በመሆናቸው መንግስት ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር ረሃብን ማጥፋት ይኖርበታል ሲሉም አክለዋል። የአፍሪካ ልማት ባንክ ተጠሪ ዶክተር አብዱል ካማራ 'በአፍሪካ ድህነትን በመቀነስ ረሃብን ለማጥፋት በተለያዩ የመሰረተ ልማት ዘርፎች ድጋፍ እናደርጋለን' ብለዋል። አገራት በኢንዱስትሪ ፓርኮች፣ በኤሌክትሪክ ማስፋፊያ፣ በግብርናና በሌሎች የመሰረተ ልማት ዘርፎች የሚያደርጉት የፋይናንስና የቴክኒክ ትብብር ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ተናግረዋል። በኢትዮጵያ ብሎም በአፍሪካ ድህነትና ረሃብን ለማጥፋት ከዓለም አቀፍና አህጉራዊ ተቋማት ጋር በቅንጅት እንደሚሰሩም አክለዋል። ግብርናውን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ፣ የአመጋገብ ልምድን ማሳደግ፣ ድህነትን ማጥፋት፣ ማህበራዊ ጥበቃ ማድረግና የአስቸኳይ ጊዜ ዝግጁነትና አደጋ መከላከል ቅድሚያ ሊሰጣቸው እንደሚገባም ዶክተር አብዱል ካማራ አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም