የስፖርት ቤተሰቦች በሜዳ ላይ የሚከሰቱ ግጭቶችን በማስወገድ የሰላም አቀንቃኝ ሊሆኑ ይገባል

62
አዲስ አበባ ታህሳስ 3/2011 የስፖርት ቤተሰቦች በሜዳ ላይ የሚከሰቱ ግጭቶችን በማስወገድ የሰላም አቀንቃኝ እንዲሆኑ የሰላም ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሙፈሪሃት ካሚል ጥሪ አቀረቡ። ስፖርት የሰላምና የፍቅር ምንጭ መሆኑን ማሳየትና ጥላቻን ድል መንሳት እንደሚጠበቅባቸውም አስገንዝበዋል። "የስፖርት ቤተሰብ ለሰላም" በሚል መሪ ሃሳብ ስፖርት የአገርን ሰላም በማረጋገጥ በሚኖረው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ላይ ያተኮረ ውይይት ተካሂዷል። የስፖርት ማህበረሰቡን ያሳተፈውን መድረክ የባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ሚኒስቴር ከሰላም ሚኒስቴር ጋር በመሆን አዘጋጅቶታል። የሰላም ሚኒስትሯ በውይይቱ ላይ ስፖርት ሰላምና ፍቅርን የሚሰብክ፣ መተባበርን፣ አብሮነትና አንድነትን የሚያጠናክር መድረክ መሆኑን ገልጸዋል። በአገር ኢኮኖሚ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ እድገት የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ እንደሆነም ተናግረዋል። "በአላስፈላጊ ግጭቶችና ብጥብጦች የሚታጀብ ከሆነ ግን ስፖርት የሰላምና የፍቅር መድረክ ሳይሆን የጥላቻና የሰቀቀን መገለጫ ይሆናል" ነው ያሉት። ስፖርት በጋራ የሚቋደሱት የሰላምና የአንድነት ማዕድ መሆኑን በመገንዘብ የሚገባውን ክብር በተግባር ማረጋገጥ እንደሚገባም አክለዋል። ሚኒስትሯ በስፖርት ሜዳ ላይ የሚከሰቱ ግጭቶችን በማስወገድ፣ ተፈጥሯዊ ባህሪውን በማክበርና ጥላቻን ድል በመንሳት ሁሉም የስፖርት ቤተሰቦች የሰላም አቀንቃኝ እንዲሆኑም ጥሪ አቅርበዋል። የባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ሚኒስትሯ ዶክተር ሂሩት ካሳሁን በበኩላቸው በቡድንም ሆነ በግል ተሳትፎ ውጤት ለማምጣት ስፖርታዊ ጨዋነት እንደሚያስፈልግ አንስተዋል። ይህን ማረጋገጥ የሚቻለው ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል በጥምረት መስራት ሲችል እንደሆነም አመልክተዋል። ስፖርት ያለ ተመልካች ደህንነትና ምቹ ሁኔታ ትርጉም አልባ በመሆኑ የዘርፉ አመራሮች፣ አሰልጣኞች፣ ክለቦችና ደጋፊዎች የበኩላቸውን  መወጣት እንደሚገባቸውም አስገንዝበዋል። በውይይቱ "ስፖርት ለሰላም" በሚል ርዕስ ጽሁፍ ቀርቦ ውይይት የተካሄደበት ሲሆን ህብረተሰቡን ማስተማር የሚያስችሉ መሰል መድረኮች መቀጠል እንዳለባቸው ከተሳታፊዎች አስተያየት ተሰጥቷል። በውስን ጊዜ ከጥቂት የስፖርት ቤተሰቦች ጋር የሚካሄድ ውይይት ብቻውን ውጤት ስለማያመጣ ብዙሃኑን መሰረት ያደረገ ስራ መስራት እንደሚገባም ተጠቁሟል። ተሳታፊዎቹ በስፖርት ሜዳ ላይ ችግሮች እንዳይፈጠሩና ሰላማዊነቱ እንዲጠበቅ በማድረግ ረገድ የድርሻቸውን ለማበርከት ጥረት እንደሚያደርጉም ተናግረዋል። የስፖርት ፌዴሬሽኖች፣ ምሁራንና ከተለያዩ ክልሎች የተውጣጡ የስፖርት ማህበረሰቦት በውይይቱ ተሳትፈዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም