የፈረንሳዩ ፕሬዘዳንት ዝቅተኛ ወርሃዊ የደመወዝ ጣሪያ በ100 ዩሮ እንዲያድግ ወሰኑ

58
ታህሳስ 2/2011 ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ዝቅተኛ የወር ደመወዝ ጣሪያ በ100 ዩሮ እንዲጨምር መወሰናቸውን ትናንት በቴሌቪዥን ባደረጉት ንግግር ይፋ አድርገዋል። የፓሪስና ሌሎችም ከተሞች ጎዳናዎች “ቢጫ ሰደርያ” የሚል ስያሜ የተሰጠውን የተቃውሞ እንቅስቃሴ ለሳምንታት አስተናግደዋል።
የፈረንሳይ መንግስት በነዳጅ ሽያጭ ላይ ታክስ ለመቁረጥ መወሰኑን ተከትሎ የተቀሰቀሰው ተቃውሞ አቅጣጫውን የመንግስትን ፖሊሲዎች ወደ መቃወም ቀይሯል። ማህበራዊ እና ኢኮኖያዊ ፍትህ የለም ያሉት የሀገሪቱ ዜጎች ከፖሊስ ጋር ግብግብ ሲገጥሙ ተስተውሏል። ትናንት ምሽት በቴሌቪዥን ቀርበው ብሔራዊ ንግግር ያደረጉት ፕሬዚዳንት ማክሮን ከፈረንጆቹ 2019 ጀምሮ ዝቅተኛ የደመወዝ ጣሪያ በ100 ዩሮ እንደሚጨምር ተናግረዋል። ከመደበኛ የስራ ሰዓት በተጨማሪ በሚሰሩ ስራዎች ከሚገኝ ገቢ ታክስ እንዳይቆረጥ እንደሚደረግ ቃል ገብተዋል። ከ2 ሺህ ዩሮ በታች ጡረታ ከሚያገኙ ሰዎች የሚቆረጠው የማህበራዊ ዋስትና ክፍያ ጭማሪ እንዲሰረዝ መወሰናቸውን ጠቁመዋል። የፈረንሳይ መንግስት በነዳጅ ላይ ሊጥል የነበረውን የግብር ጭማሪ ባሳለፍነው ሳምንት መሰረዙ ይታወቃል። በፈረንሳይ የተቀቀሱ ተቃውሞዎችን 84 በመቶ ዜጎች (በብዛት መካከለኛ ገቢ ያላቸው ቡድኖች) እንደደገፏቸው የዳሰሳ ጥናቶች ያሳያሉ። ማክሮን በንግግራቸው የግል ቀጣሪዎችም ከቻሉ ለሰራተኞቻቸው ዓመታዊ ቦነስ (ማበረታቻ ክፍያ) እንዲሰጡ ጠይቀዋል። ላለፉት አንድ ዓመት ተኩል በሌሎች ጉዳዮች ላይ በማተኮራችን ለዜጎቻችን ትኩረት አልሰጠንም፤ ከአዲሱ ዓመት ጀምሮ ዜጎቻችንን የሚጠቅሙ ማህብራዊና ኢኮኖሚያዊ መረጋጋትን የሚፈጥሩ ስራዎችን እንሰራለን ነው ያሉት። በፈረንሳይ ለአራት ሳምንታት የዘለቀው ተቃውሞ በኢኮኖሚዋ ላይ 1 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር ኪሳራ ማድረሱና ለሰዎች ህይወት ህልፈት ምክንያት መሆኑ ተነግሯል። ምንጭ፦ሮይተርስና አልጀዚራ
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም