ምክር ቤቱ የምግብና መድሃኒት አስተዳደር ረቂቅ አዋጅን አይቶ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ መራ

78
አዲስ አበባ ታህሳስ 2/2011 የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የምግብና መድሃኒት አስተዳደር ረቂቅ አዋጅ አይቶ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ መራ። ምክር ቤቱ የ4ኛ የሥራ ዘመን 11ኛ መደበኛ ስብሰባውን ዛሬ አካሄዷል። በዚህም ለስምንት ዓመታት ሲሰራበት የቆየው የምግብና መድሃኒት አስተዳደር አዋጅን የሚተካ አዲስ አዋጅ በማየት ለሚመለከተው አካል መርቷል። የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር አቶ ጫላ ለሚ የረቂቁን ማብራሪያ ሲያቀርቡ እንዳሉት ነባሩን አዋጅ መቀየር ያስፈለገው የቁጥጥር ስራውን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስና በመስኩ ያለው የቴክሎጂ አጠቃቀም ከፍ ወዳለ ደረጃ ለማሸጋገር ነው። ጤንነቱ ባልተጠበቀ ምግብና መድሃኒት ምክንያት የህብረተሰቡ ጤና አደጋ ላይ እንዳይወቅድ መከላከልም የአዲሱ አዋጅ ቁልፍ ዓላማ መሆኑን ነው ያብራሩት። ከዚህ ባለፈም አዋጁ ደህንነቱና ውጤታማነቱ ባልተረጋገጠ የህክምና መሳሪያ ሳቢያ የሰው ህይወት ላይ የሚደርሰውን የጤና ችግር መከላከልና መቆጣጠር ታሳቢ ያደረገ መሆኑን ጠቁመዋል። ከዚህም በላይ የህክምና መሳሪያ ፣ የውበት መጠበቂያና የትንባሆ አስተዳደር ስርዓትን መዘርጋት የሚያስችል የሕግ ማዕቀፍ አስፈላጊ በመሆኑም ነው ረቂቅ አዋጁ የተዘጋጀው ሲሉ ነው ያብራሩት። አዋጁ የምግብ ደህንነትን በሚመለከት 15 ድንጋጌዎችን የያዘ ሲሆን የመድሃኒትና የህክምና መሳሪያ ደህንነት ጥራትና ፈዋሽነት ላይ ደግሞ ተጨማሪ 15 ድንጋጌዎችን አካቷል። እንደ አቶ ጫላ ማብራሪያ ረቂቅ አዋጁ አደገኛ ኬሚካሎችን በማዘጋጀት፣ በማጓጓዝና በማከማቸት ሥራ ላይ የተሰማራ ማንኛውም ሰው የኀብረተሰብ ጤና ላይ ጉዳት እንዳያስከትል መስፈርቶችን የሚያስቀምጥ ነው። በዚህ መሰረት በፊት የነበረው አዋጅ ቁጥር 661/2002/ ሙሉ በሙሉ የሚተካ እንደሆነም አስታውቀዋል። የምክር ቤቱ አባላት በበኩላቸው አዋጁ በአዲስ መልክ መዘጋጀቱ መልካም ቢሆንም በተለይ ቅጣትን በተመለከተ የተደነገገው ምን ያህል አስተማሪ ነው? የሚለው ሊፈተሽ ይገባል ብለዋል። "በሚሊዮን ለሚያተረፉ ነገዴዎች 50 ሺህ ብር ቅጣት መጣል ምን ያህል ውጤት ያመጣል? ይሄንን መለስ ብሎ መቃኘት ያስፈልጋል" ሲሉም ጠቁመዋል አባላቱ። ከአልኮል ጋር በተያያዘም በቅርቡ የአልኮል ማስታወቂያዎች ከምሽቱ 3 ሰዓት እስከ ንጋቱ 12 ሰዓት ብቻ ማስታወቂያ እንዲቀርብ የወጣው ክልከላ ለውጥ ያመጣል የሚል ግምት የለንም፤ ለውጥ እንዲመጣ ከታሰበ የማስታወቂያው ይዘት ላይ ትኩረት ማድረግ ይገባል ነው ያሉት አባላቱ በሰጡት አስተያየት። የቁጥጥር ሥራውን በተመለከተ መስሪያ ቤቱ ውጤታማ እንዲሆን ከተፈለገ በሰው ኃይልና በአደረጃጀት መጠንከር አለበት ያሉ የምክር አባላትም ነበሩ። በተለይ ደግሞ አደንዛዥ እጽ ላይ ፍቃድ ወስደው የሚሰሩ አሉ፤ ከሚያመጣው ጉዳት አንጻር በምን መልኩ ነው የሚታየው? የሚለው በዝርዝር መተያት እንደሚኖርበት አጽንኦት የሰጡ የምክር አባላትም አልጠፉ። ምክር ቤቱ አዋጁን ከመረመረ በኋላ በዋናነት ለሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ እንዲሁም ለንግድና እንዲስትሪ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ደግሞ በተባባሪነት ለዝርዝር ዕይታ መርቷል። በተመሳሳይም ምክር ቤቱ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ማቋቋሚያ አዋጅ ለማሻሻል የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ መርምሮ ለሰው ኃብትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቷል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም