በኢትዮጵያ አማካይ የኤች አይ ቪ/ኤድስ ስርጭት 0.9 በመቶ መድረሱን ጥናት አመለከተ

120
አዲስ አበባ  ታህሳስ 1/2011 በኢትዮጵያ አማካይ የኤች አይ ቪ/ኤድስ ስርጭት 0.9 በመቶ መድረሱን ጥናት አመለከተ። ጥናቱ የተካሄደው በዋናነት በኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ሲሆን ጤና ሚኒስቴር፣ የአሜሪካ መንግስት የበሽታ መቆጣጠርና መከላከል ማዕከል፣ የኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ አይካፕ፣ የኤች አይ ቪ/ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ጽህፈት ቤትና ሌሎች መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ አጋር አካላት ነው። ጥናቱን አስመልክቶ የጤና ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩትና አጋር አካላት በጋራ በመሆን ዛሬ ጥናቱን ይፋ አድርገዋል። የጤና ሚኒስትሩ ዶክተር አሚር አማን በዚሁ ግዜ እንደተናገሩት በዛሬው እለት ይፋ የሆነው የኤች አይ ቪ ስርጭት ላይ ያተኮረው ይህ ጥናት ከስድስት እስከ ሰባት ወራት ፈጅቷል። ጥናቱ በአራት ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ በማተኮር የተካሄደ እንደሆነና አገሪቷ በአሁኑ ወቅት ላይ የኤች አይ ቪ/ኤድስ የስርጭት ምጣኔውን ከማወቅ ባሻገር ህብረተሰቡ ይህንን እንዲያውቅ ለማስቻልም ያለመ ነው። ለዚህም ደግሞ ከተሞች ላይ ትኩረት ያደረገና እድሜያቸው ከ0 እስከ 15 ያሉ ታዳጊዎችና ከ50 እስከ 64 የእድሜ ክልል ባሉ ዜጎች ላይ ያተኮረ እንደሆነ ነው የተናገሩት። በተጨማሪም ቀደም ሲሉ በነበሩ ጥናቶች መሰረት ሴቶች ለቫይረሱ ተጠቂ መሆናቸውን ተከትሎ በዚሁ ጥናት ላይም ሴቶች ላይ ትኩረት መደረጉንም እንዲሁ። ሌላው በጥናቱ መሰረት ከቫይረሱ ጋር ተያያዥ የሆኑ ሄፓታይተስ ቢ እና ሲን በሚመለከት በጥናቱ መካተቱንም ሚኒስትሩ አክለዋል። በዚህም ከ50 እስከ 64 የእድሜ ክልል ባሉ ዜጎች የቫይረሱ ምጣኔ 4.4 ሲሆን በአጠቃላይ በከተሞች ሶስት በመቶ ነው ብለዋል። ከ0 እስከ 15 ያሉ ታዳጊዎች እንዲሁ 0.3 ወይም 19ሺህ ህጻናተ የቫይረሱ ተጠቂዎች እንደሆኑም ጥናቱ ያመላክታል ሲሉ ተናግረዋል። በዚህም በኢትዮጵያ አማካይ የኤች አይ ቪ/ኤድስ ስርጭት 0.9 መሆኑ የተመላከተ ሲሆን ይህ አሃዝ በከተሞች 3 በመቶ የምጣኔ ደረጃ ላይ መሆኑ በጥናቱ ተገልጿል። የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጄነራል ዳይሬክተር ዶክተር ኤባ አባተ በበኩላቸው ጥናቱ በከተሞች  የተካሄደበት ምክንያት ቀደም ሲል የተሰሩ ጥናቶች በገጠራማ አካባቢዎች ያለው የኤች አይ ቪ/ኤድስ ስርጭት ዝቅተኛ በመሆኑ በከተሞች  ደረጃ  ለማወቅ እንደሆነም ገለጸዋል። በተጨማሪም ቫይረሱ በደማቸው ካለባቸው 610 ሺህ 335 ዜጎች ሁለት ሶስተኛው የሚኖሩት በከተሞች መሆናቸውን ተከትሎ ነው ብለዋል። ጥናቱ ከ15 እስከ 64 የእድሜ ክልል ባሉ ዜጎች 10 ሺህ 529 የከተማ ቤቶች ውስጥ በሚኖሩ 20 ሺህ 170 ዜጎችን ተሳታፊ አድርጓል። በ2020 በተያዘው እቅድ 90 በመቶ ያክል ዜጎች ተመርምረው ራሳቸውን እንዲያውቁ፣ 90 በመቶ ያክሉ በደማቸው መኖሩን የሚያውቁና ለራሳቸው በሚያደርጉት እንክብካቤ ከደማቸው ውስጥ ቫይረሱን እንዲቀንሱ፣ 90 በመቶ በጥንቃቄ የቫይረሱን መድኃኒት እንዲወስዱ ይደረጋል በተባለው የሶስቱ 90 እቅዶችን ከግብ ለማድረስ እየተሰራ ነው ብለዋል። በዚህም 71 በመቶ የሚሆኑት በአሁኑ ወቅት ተመርምረው ራሳቸውን ያወቁ ሲሆኑ 90 በመቶ ለማድረስ ብዙ መስራት ይጠበቃል ነው ያሉት። ሁለቱ 90 በመቶዎች ግን አሁን ካለው ጋር ሲነጻጸር በጣም መሰራት እንዳለበት ጥናቱ ያመላክታል ሲሉ አስገንዝበዋል። ይሁን እንጂ በዓመት የኤች አይ ቪ/ኤድስ ስርጭት ከነበረበት 81ሺ በአሁኑ ወቅት ወደ 15 ሺህ ዝቅ ማለቱን ጠቁመዋል። በጥናቱ ከ1ሺህ በላይ ባለሙያዎች የተሳተፉ ሲሆን ከስድስት እስከ ሰባት ወራትን መፍጀቱንም በመግለጫው ተነግራል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም