የአምናው የሊጉ አሸናፊ ወላይታ ድቻ የቮሊቦል ፕሪሚየር ሊጉን በድል ጀምሯል

63
አዲስ አበባታህሳስ 1/2011 ወላይታ ድቻ ጣና ባህርዳርን በማሸነፍ የ2011 ዓ.ም ሐበሻ ሲሚንቶ የወንዶች ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ ውድድርን በድል ጀምሯል። የፕሪሚየር ሊጉ የሁለተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ትናንት በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች ተካሂደዋል። ወላይታ ድቻ በባህርዳር ሚሊኒየም ሜዳ በተደረገው በአራት የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ጣና ባህርዳርን 3 ለ 1 በሆነ ውጤት አሸንፏል። በመጀመሪያ ሳምንት የሊጉ መርሃ ግብር ሶዶ ላይ ወላይታ ድቻ ከአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን ሊያደርጉት የነበረው ጨዋታ አዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባቀረበው ጥያቄ ላልተወሰነ ጊዜ መራዘሙ ይታወቃል። በሊጉ በመሳተፍ እንግዳ የሆነው አዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ በአዲስ አበባ ትንሿ ስታዲየም በመከላከያ 3 ለ 2 በሆነ ውጤት ተሸንፏል። መከላከያ እስካሁን በተካሄዱ የሊጉ ውድድሮች ሁለት ጨዋታዎችን ማሸነፍ ችሏል። በትንሿ ስታዲየም በተካሄደ ሌላ ጨዋታ ሙገር ሲሚንቶ ፌዴራል ማረሚያ ቤቶችን 3 ለ 1 በሆነ ውጤት ረቷል። ባሌ ሮቤ ላይ አዲስ አበባ ፖሊስን ያስተናገደው መዳ ወላቡ ዩኒቨርሲቲም 3 ለ 0 አሸንፏል። የ2011 ዓ.ም የሐበሻ ሲሚንቶ የወንዶች ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ የሶስተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ከሁለት ሳምንት በኋላ ይካሄዳሉ። በሐበሻ ሲሚንቶ የወንዶች ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ ስምንት ክለቦች ይሳተፋሉ።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም